
አዲስ አበባ: የካቲት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በወላይታ ሶዶ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው 9ኛው የከተሞች ፎረም የመዝጊያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
በመዝጊያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ተስፋዬ ይገዙ “በከተማችን የተካሄደው ፎረም የልምድ እና የባሕል ግብይት የተከናወነበት ነበር” ብለዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የኅብረ ብሔራዊነት እናት በኾነችው ወላይታ ሶዶ የተሠባሠቡ ሁሉ ባሕል እና እሴታቸውን፤ ልምድ እና እውቀታቸውን የተገበያዩበት፤ ኅብረ ብሔራዊ መልኮቻቸውንም ያሳዩበት ነበር ነው ያሉት።
እንዲህ ዓይነት መድረኮች ሀገረኛ የብዝኀነት መልኮችን ድምቀት የሚያሳዩ መኾናቸውን ያነሱት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ እንደ ክልል የተሰጠው ትኩረት ትልቅ እንደነበርም አስረድተዋል።
ዝግጅቱ ስኬታማ እንዲኾንም ሕዝቡ፣ የመንግሥት አመራር እና ሙያተኞች ሁሉ ብርቱ አቅም ነበራችሁ ለዚህም ክብር ይገባችኋል ብለዋል። የክልሉ መንግሥት በቀጣይም እንዲህ ዓይነት የውስጥ አቅሞችን በሚያጠናክሩ እና ሀገረኛ መልኮችን በሚያደምቁ ሁነቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራም ነው ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ያብራሩት፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ “የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም መርሐ ግብር መካከለኛውን እና አሠባሣቢውን ትርክት በመፍጠር ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው” ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዲህ ዓይነት መድረክ እና ፎረሞች ላይ በምግብ ዋስትና እና የሴፍትኔት ተግባራት፣ በከተማ ነዋሪዎች የአገልግሎት ቅልጥፍና፣ የከተሞች የአረንጓዴ ልማት እና መሰል የከተሞች የለውጥ ተግባራትን ለመተግበር መትጋት ይጠይቀዋል ብለዋል።
ዘጠነኛውን የከተሞች ፎረም ጨምሮ የእስካሁኖቹ ውጤታማ ነበሩ ያሉት ሚኒስትሯ 10ኛው የከተሞች ፎረም ደግሞ በአፋር ሰመራ ከተማ እንዲከበር ተመርጧል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!