
ባሕር ዳር: የካቲት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት በ6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ፣ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ የዳኞችን ሹመት መርምሮ አጽድቋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቡየ ካሳሁን የዳኞችን ሹመት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ለሹመት ካቀረቧቸው ዳኞች መካከል ሁለት የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች እና 154 የወረዳ ፍርድ ቤት ረዳት ዳኞች ይገኙበታል። በዚህም መሠረት አቶ ባየ ጌታቸው ፈንታ የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና አቶ ዮሀንስ ወንድሙ ደስታ የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ኾነው እንዲሾሙ ቀርበዋል።
የ154ቱ የወረዳ ፍርድ ቤት ረዳት ዳኞች ሥም ዝርዝርም ለምክር ቤቱ ቀርቧል። በዚህም መሠረት የምክር ቤት አባላት በዳኞች ሹመት ላይ ተወያይተዋል። የዳኞች ተረጋግቶ አለመሥራት እና ፈጥኖ ሥራ መልቀቅ ምክንያቱ ተጠንቶ መፍትሔ መሰጠት አለበት የሚል ሃሳብ በምክር ቤት አባላት ተነስቷል።
በመጨረሻም የሁለቱም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች እና የ154 የወረዳ ረዳት ዳኞች ሹመት በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
