
ደሴ: የካቲት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ዓድዋን ለዘላቂ ሰላም እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ የወጣቶች ኮንፈረንስ በደሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በደሴ ከተማ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶች በተሳተፉበት ኮንፈረንስ 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል ታስቧል፡፡
ለጥቁር ሕዝብ የድል ጮራ የፈነጠቀው የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በአንድነት፣ በመተባበበር እና በአልበገር ባይነት መንፈስ የተዋደቁበት እንደነበርም ተወስቷል፡፡
ዓድዋ ሲነሳ አልሸነፍ ባይነትን እና ከምንም በፊት ለሀገር ቅድሚያ መስጠትን እናስታውስበታለን ያሉት አሚኮ ያነጋገራቸው ወጣች ዛሬም በየተሰማራንበት የሙያ ዘርፍ የራሳችንን ታሪክ አስቀምጠን ማለፍ አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ወጣቶች ምክንያታዊ በመኾን የሀገር ሰላም እንዲጠበቅ የበኩላቸውን መወጣት እንደለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት የሥራ እድል በመፍጠር የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ እንደሚገባም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰይድ አራጋው ወጣቱ ትውልድ ከዓድዋ ድል ታሪክ መደማመጥን እና አንድነትን በመውሰድ ሀገር ላይ ያለውን ችግር በጋራ መወጣት ይገባልዋል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ተሾመ ፈንታው ወጣቶች ከዓድዋ ድል የአባቶችን የአንድነት እና ለሀገር የከፈሉትን መሥዋዕትነት በመውረስ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
የወጣቶች ጥያቄ የሚመለሰው ሀገር ሰላም ስትኾን ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!