በአንድ ቀን ጫጩት ማሳደግ ሥራ ውጤታማ መኾን መቻላቸውን በደባርቅ ከተማ በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች ተናገሩ

52

ደባርቅ: የካቲት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ ግብርና በጠባብ ቦታ ቴክኖሎጅን በመጠቀም የሚሠራ ተግባር ነው። ተግባሩ በውጤታማነት ከተፈጸመ በምግብ ራስን ለመቻል፣ የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ እና ለሌሎች ጉዳዮች ጉልህ ሚና ይኖረዋል። በከተማ ግብርና ከሚጠቀሱ ተግባራት መካከል የዶሮ እርባታ ተጠቃሽ ነው።

ወጣት ግሩም ወረታው እና ዮናስ አዳነ በደባርቅ ከተማ የአንድ ቀን ጫጩት በማሳደግ ሥራ የተሰማሩ ወጣቶች ናቸው። ወጣቶቹ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአንድ ቀን ጫጩት ከፋብሪካ ተረክበው እስከ 45 ቀን ካሳደጉ በኋላ ለከተማው ማኅበረሰብ ይሸጣሉ።

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ሥራውን እንደጀመሩ የሚናገሩት ወጣቶቹ በአግባቡ ከተሠራ አዋጭ የሥራ ዘርፍ መኾኑን ተናግረዋል። ከትንሽ ነገር ተነስተን የተሻለ ደረጃ ደርሰናልም ብለዋል።
ይሁን እና የመሥሪያ ቦታ አለመኖር፣ የብድር አገልግሎት ችግር፣ የጫጩት አቅርቦት እና ሌሎች ችግሮች በፈለግነው ልክ ውጤታማ እንዳንኾን አድርጎናል ብለዋል።

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር እንሰሣት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መላኩ ገብረሥላሴ በከተማ አሥተዳደሩ በዶሮ እርባታ የተሰማሩ 32 ኢንተርፕራይዞች እንደሚገኙ አመላክተዋል።

በዘርፉ የተሰማሩት ወጣቶች ጫጩት፣ የእንቁላል እና የሥጋ ዶሮ ለዞኑ ኹሉም አካባቢዎች በማሰራጨት የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

አቶ መላኩ ወጣቶቹን የገበያ ትስስር በመፍጠር እና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ እያገዙ መኾኑን አንስተዋል። የሚያነሱትን የቦታ እና የብድር አቅርቦት ችግር ለመፍታትም ከከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ መኾናቸውን እና ችግሩም እንደሚቀረፍ አረጋግጠዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን እንሰሣት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ፍቅሩ ስመኝ በዞኑ በአንድ ቀን ጫጩት ማሳደግ የተደራጁ 37 ኢንተርፕራይዞች እንደሚገኙ ተናግረዋል። ከፕሮጀክቶች ጋር በመቀናጀትም ወጣቶቹን ለማገዝ እና ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ እንደኾነ አንስተዋል።

ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ችግር ለመፍታት ከኢትዮ ችክን ጋር መነጋገራቸውን ያነሱት ኀላፊው ኩባንያው ያለበትን ችግር እንዲቀርፍ መግባባት እንደቻሉም ጠቁመዋል።
የዶሮ እርባታውን በኹሉም የዞኑ አካባቢዎች በማስፋት የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለመሙላት እና ተግባሩን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠሩም አቶ ፍቅሩ አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፀጥታ ችግሩን ለመፍታት ቀዳሚ መንገዳችን ሰላማዊ አማራጮችን መከተል ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“የጋራ ትርክት የኾነውን ኅብረ ብሔራዊነት እያጎለበትን እንቀጥላለን” የወላይታ ዞን አሥተዳዳሪ