
ባሕር ዳር፡ የካቲት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው። በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ በመንግሥት በኩል ያለው የሰላም ቁርጠኝነት ምን እንደሚመስል የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ “የክልሉም ይሁን የፌዴራል መንግሥት ማንኛውም ችግር በሰላም ብቻ እንዲፈታ ፅኑ ፍላጎት አላቸው” ሲሉ ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት ችግሮች በሰላም እና በውይይት እንዲፈቱ በክልሉ ምክር ቤት ጭምር የሰላም ጥሪ አስተላልፎ እንደነበርም አስታውሰዋል። ይሁን እንጅ ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚገኝ አለመኾኑ ጠቁመዋል።
ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር ክልሉ ያስተላለፈው ይፋዊ የሰላም ጥሪም መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል። የሰላም ጥሪው ለጥፋተኞች ምህረት የሚያስገኝ እና በሰላም ሠርቶ የመለወጥ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል። ይህን እድል በመጠቀም በርካታ ወጣቶች ወደ ሰላም መመለሳቸውን፣ ራሳቸውን በሚጠቅም ሥራ ላይ ተሰማርተው ሕዝባቸውን እና ክልሉን በልማት ለመካስም የተሐድሶ ሥልጠና ወስደው መዘጋጀታቸውን ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል። እነዚህ ወጣቶች የመንግሥትን ጥሪም በማድመጥ፣ ለክልሉ እና ለሕዝባቸውም ሰላም በማሰብ ከጥፋት አካሄድ የተመለሱ የሰላም ጀግኖች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
መንግሥት ያስተላለፈው የሰላም ጥሪ “እጅ ስጡ ተባልን” የሚል የተዛባ ትርጉም በመስጠት አሁንም ድረስ በጥፋት ድርጊት ላይ የሚገኙ አካላት እንዳሉም ጠቁመዋል። እነዚህ አካላት አሁንም ድረስ ሕዝቡ እንደልብ ከቦታ ቦታ እንዳይነግድ እና እንዳይሠራ መንገድ እየዘጉ እንደሚገኙም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል። ይሕን ሕዝብን የሚበድል ተግባር በቅንጅት በመከላከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ወቅቱ ለአርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ ለማድረስ በከፍተኛ ትኩረት የማጓጓዝ ተግባር የሚከናወንበት እንደኾነ ጠቅሰው በነጻ አውጭ ስም የአርሶ አደሩን ማዳበሪያ ለመዝረፍ የሚሞክሩ መኖራቸውን ገልጸዋል። ይህ አካሄድ አርሶ አደሩ እንዳያመርት እና የክልሉም ኢኮኖሚ እንዳይሻሻል የሚደረግ የተሳሳተ እሳቤ እና ድርጊት በመኾኑ መታገል ግድ ይላል ነው ያሉት።
በክልሉ ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ሕዝቡም በነጻነት ተዘዋውሮ እንዲሠራ እና ተወዳዳሪ እንዲኾን ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን እንሠራለን ነው ያሉት። “ለሰላማዊ አማራጮች በሙሉ በራችን ክፍት ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አሁንም ቢኾን ከጥፋት ድርጊት ተመልሶ ሰላምን የሚመርጥ ካለ ለመነጋገር እና ለመወያየት ዝግጁ ነን ብለዋል።
“የፀጥታ ችግሩን ለመፍታት ቀዳሚ መንገዳችን ሰላማዊ አማራጮችን መከተል ነው” ሲሉም ተናግረዋል። የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በማጣጣል እና አልባሌ ትርጉም በመስጠት በጥፋት መንገድ ለሚቀጥሉ አካላት ደግሞ እንደመንግሥት ሕግ የማስከበር ግዴታችንን በጥንካሬ እንወጣለን ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!