የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስከብሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተከናውነዋል።

19

ባሕር ዳር: የካቲት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስከብሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ.ር) በሳምንታዊ መግለጫቸው ከአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በተጓዳኝ ከሀገራት ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ውይይቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአንጎላ እና ደቡብ አፍሪካ ጋር የተፈረሙ ስምምነቶች ትልቅ ስኬት መኾናቸውን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ወደከፍታ እየወጣ መኾኑ የታየበት ሳምንት ነበር ብለዋል።

ታሪካዊ ወዳጅነት ካላት ዝምባብዌ ጋር ውጤታማ ምክክር መደረጉን ገልፀው በግብርና እና ሌሎችም መስኮች በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ ስለመደረሱ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል እንደቤተሰብ የሚተያይ ሕዝብ ያላቸው ኢትዮጵያ እና ኬንያ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ መካሄዱን ጠቅሰው ሁለቱ ሀገራት በሰባት ዘርፎች ስምምነት ማድረጋቸውን ነው የጠቀሱት።

ስምምነቱም በቱሪዝም፣ ባሕልና ስፖርት፣ በዱር እንስሳት ጥበቃ፣ በዓሳ ልማት፣ ፔትሮሊየም እና በማረሚያ ቤት አገልግሎት እና በሲቪል ሰርቪስ አቅም ግንባታ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የቪዛ ጉዳይ ሌላው የስምምነት ጉዳይ መኾኑን ጠቅሰው ከ1958 ጀምሮ የተደረገው የቪዛ ነፃ ስምምነት በኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መልኩ እንዲኾን መከለሱን ነው ያነሱት።
ይህም ለዘመናት የነበረውን ወዳጅነት ይበልጥ ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሳድግ ገልፀዋል።

የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት በመንግሥት ለውጥ የማይዋዥቅ እንደኾነ ገልፀው፣ ወዳጅነታቸው በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል። ከሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች ጋር በተደረገ ውይይት ሀገራቱ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እንዲፀና ፍላጎት ማሳየታቸውን እና ኤምባሲዎቻቸውን ለማጠናከር መወሰናቸውን ገልፀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ኮንፍረንስ በሰመራ መካሄድ ጀመረ።
Next article“ከኦሮሚያ ክልል ከሁሉም ዞኖች ከተወጣጡ ተወካዮች ጋር ተወያይተናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)