“የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የባሕር በር ስምምነት በሦስተኛ አካላት አይቀየርም” ዒሳ ካይድ መሐሙድ(ዶ.ር)

43

ባሕር ዳር: የካቲት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የባሕር በር ስምምነት በሦስተኛ አካላት ተፅእኖ ሊቀየር እንደማይችል የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዒሳ ካይድ መሐሙድ(ዶ.ር) ገለጹ።

በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር ኢሳ ካይድ መሐሙድ ሶማሊላንድ ከዐረብ ሊግ እና ከግብጽ የሚወጡ መግለጫዎች አያሳስባትም ብለዋል።

ምክንያቱም አሉ ዶክተር ዒሳ ካይድ መሐሙድ በሶማሊላንድ እና በኢትዮጵያ መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች በሦስተኛ አካላት ሊቀየሩ ወይም ሊለወጡ አይችሉም ብለዋል። ሚኒስትሩ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የባሕር በር ስምምነት በተመለከተ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን እንደምትቃወምም ተናግረዋል። እንዲኹም ሂደቱ በውጭ አካላት እንደማይቀየር ዶክተር ኢሳ ገልጸዋል፡፡ ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ የተፈራረሙት የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ነው ብለዋል።

ሥምምነቱን ዳር የሚያደርስ ቴክኒካል ኮሚቴ ማዋቀር፣ ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ማደራጀት እና ከፍተኛ የሕገ መንግሥት አማካሪ ግብረ ኃይል የማደራጀት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ቡድኑ የስምምነቱ ሂደት እና ሕግ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን እያከናወነ ነው። ይህም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና ለሁለቱም ሀገራት አብሮ የማደግ ዕድል ይዞ የሚመጣ ይሆናል ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ ድንበር በመኖሩ የሕዝብ ለሕዝብ ውህደት መኖሩን የገለጹት ዶክተር ኢሳ ይህም ግንኙነት ከመግባቢያ ሰነዱ በኋላ አልተጀመረም፤ ይልቁንም ረጅም ጊዜ የቆየ እና የሚቀጥል ነው ብለዋል። ሥምምነቱ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ነው። ይህም የሁለቱን ሀገራት ንግድ እና አጠቃላይ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ያሳድጋል ብለዋል።

የኢትዮ-ሶማሊላንድ የመግባቢያ ሥምምነት ከዓለም አቀፍ ሕግ እና ከሁለትዮሽ የንግድ እንቅስቃሴ ጋር የሚስማማ ነው ያሉት ዶክተር ዒሳ ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ሥምምነት ፍጹም ሕጋዊ እና ሕጋዊ መሠረት ያለው መኾኑን ገልጸዋል።

የበርበራ ወደብን መገልገያዎች ማስፋፋት እና ማዘመን እንዲኹም የበርበራ ኮሪደርን የማገናኘት ሥራ የጀመርነው በዚሁ መነሻ ነው ብለዋል ዶክተር ዒሳ፡፡ ይህ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚፈጀውን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ዱባይ ፖርትስ ወርልድ ጋር በትብብር እየተሠራ እንደኾነ ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የውኃ ፕሮጀክት ግንባታዎች ማኅበረሰብ መር መኾን አለባቸው” ማማሩ አያሌው (ዶ.ር)
Next articleበአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ኮንፍረንስ በሰመራ መካሄድ ጀመረ።