
ባሕር ዳር: የካቲት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ የሁለተኛ ቀን የጉባኤ ውሎ የክልሉ አስፈጻሚ አካላት ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያዎችን እየሰጡ ነው።
የአማራ ክልል ውኃ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በውኃ መሠረተ ልማቶች ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከጥያቄዎች መካከል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩ የውኃ ፕሮጀክቶች በወቅቱ አለመጠናቀቃቸው ዋነኛው ነበር።
ዶክተር ማማሩ ቢሯቸው የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን ለማሳደግ እና ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ በቻለው አቅም እየሠራ ሥለመኾኑ አብራርተዋል። የውኃ መሠረተ ልማት ላይ የተያዘ በቂ በጀት እንደሌለ አመላክተው ዘርፉን በበጀት መደገፍ እንደሚገባም በምክር ቤቱ ተናግረዋል።
በየአካባቢው ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የውኃ ፕሮጀክቶችን በ2016 በጀት ዓመት በፍጥነት ለማጠናቀቅ ቃል ተገብቶ ነበር ያሉት ቢሮ ኀላፊው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንቅፉት ስለመኾኑ አመላክተዋል። ልማት ሰላምን ይፈልጋል፤ በመኾኑም በተለይም ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ጅምር ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት።
ዶክተር ማማሩ “ውኃ የልማቶች ሁሉ መሠረት ነው” ሲሉም ገልጸዋል። በመኾኑም ባንኮች እንደሌሎች የግንባታ ዘርፎች ሁሉ ለውኃ ፕሮጀክቶች ግንባታ የብድር አገልግሎት ሊፈቅዱ ይገባል ብለዋል። ዘርፉ በቂ የፋይናንስ በጀት ተይዞለት ካልተገነባ ሽፋኑን ማሳደግ እንደሚከብድም ገልጸዋል።
የተጀመሩ የውኃ ፕሮጀክቶችን ማኅበረሰቡ የራሱ መጠቀሚያ ሃብቶች አድርጎ የመቁጠር እና የመንከባከብ ውስንነት ስለመኖሩም አንስተዋል። ይህም የፕሮጀክቶች መስሪያ ቁሳቁስ ስርቆትን እና ብልሽትን አስከትሏል ነው ያሉት።
የውኃ ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዳይፈጸሙም እንቅፋት ኾኗል ሲሉ አንስተዋል። “የውኃ ፕሮጀክት ግንባታዎች ማኅበረሰብ መር መኾን አለባቸው” ሲሉም አሳስበዋል። ማኅበረሰቡን ከሥራው እቅድ ጀምሮ ማሳተፍ እና በወጭም እንዲያግዝ ማድረግ ለፕሮጀክቱ የባለቤትነት ስሜት ኖሮት ጥበቃም እንዲያደርግለት ያስችላል ብለዋል።
ዶክተር ማማሩ የተጀመሩ የውኃ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ለማጠናቀቅ እና አዳዲስ ፍላጎቶችን በመለየት እና በመገንባት የክልሉን የመጠጥ ውኃ ሽፋን ለማሳደግ ቢሮው በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!