
ባሕር ዳር: የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወደ ውጭ ከተላከው የእንስሳት ሃብት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገልጸዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ይህንን ያሉት በክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የበጀት ዓመቱን የግማሽ ዓመት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።
ርእሰ መሥተዳድሩ እንደገለጹት በ2016 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በአማራ ክልል 1 ሺህ 215 የዳልጋ ከብት ለውጭ ገበያ ቀርቧል። 18 ሺህ 80 በግ እና ፍየሎችም ወደ ውጭ ተልከዋል። የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትም የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መደገፍ ተችሏል ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ የእንስሳት ሃብትን ለውጭ ገበያ በማቅረቡ ሂደት ውስጥ መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች በሪፖርታቸው አንስተዋል። በመተማ በኩል የተሠራው የኳራንታይን ጣቢያ ሥራ አለመጀመር እና የሕገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴ በበቂ ሁኔታ አለመገታት ከዘርፉ ውስንነቶች ውስጥ ተጠቅሰዋል።
የኳራንታይን ጣቢያው ሥራ እንዲጀምር በማድረግ እና ሕገ ወጥ ንግድን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የእንስሳት ሃብት ዘርፉን ሁነኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ማድረግ እንደሚገባም ርእሰ መሥተዳድሩ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!