“የአማራ ሕዝብ ታላቆቹን የሚያከብር ታላቅ ሕዝብ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

54

ባሕር ዳር: የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር መክረዋል፡፡
በክልሉ ያለውን የመልካም አሥተዳደር እና የመሠረተ ልማት ችግርን መሠረት ተደርጎ የሕዝቡን ችግር ለማባባስ የሚደረገው ጥረት ተገቢ አለመኾኑን ተወያዮቹ ተናግረዋል፡፡

ተወያዮቹ እንዳሉት ባለፈው ዓመት ይታይ የነበረው የማዳበሪያ እጥረት አርሶ አደሩ ጅራፍ እያጮኸ ወደ ጎዳና እንዲወጣ ማድረጉ እና ቅሬታ መፍጠሩን ነው ያስገነዘቡት፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችም ወደ ተፈናቀሉበት አካባቢ እንዲመለሱ እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡

የመደመር እሳቤን የብልጽግና አመራር እና ሕዝቡ እንዲገዛው እና እሳቤው ወደ ተግባር እንዲለወጥ ለማድረግ የተሠራው ሥራ አነስተኛ መኾኑንም ተወያዮቹ አስገንዝበዋል፡፡
ክልሉ በጦርነት የተጎዳ በመኾኑ በተለየ መታየት እና ድጋፎች ሊደረጉለት እንደሚገባም ነው የጠየቁት፡፡

የሰላም እጦቱ ሕዝቡ በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ እያደረገው እንደኾነ የገለጹት ተወያዮቹ መፍትሔው በጋራ ሊፈለግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ችግሮችን እና አሁን የተፈጠረውን አለመተማመን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም ነው የተብራራው፡፡

በክልሉ የመሠረተ ልማት ጥያቄ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለተወያዮቹ በሰጡት ምላሽ “የአማራ ሕዝብ ታላቆቹን የሚያከብር ታላቅ ሕዝብ ነው” ብለዋል፡፡

ይሁን እንጅ አሁንም ማደፍረስ የሚፈልጉ ስላሉ ያን መገንዘብ ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ችግሮችን አዳምጦ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት አንድ እርምጃ መኾኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መገንዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ችግሮች ሁሉም ጋር አሉ ብሎ በማመን ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡ ሌብነት ላይ ለማጥራት ሲሞከር አስቸጋሪ ሁኔታ ነው የተፈጠረው፤ አካውንቱ፣ መሬቱ ሊበረበር እንደሚችል ሲታወቅ ውስብስብ ችግር እንደተፈጠረ ነው ያስረዱት፡፡

ሕዝብ ሰላምን ለማጽናት ወሳኝ መኾኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጥፊዎችን ከመደበቅ ወጥቶ አጋልጦ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ተፈናቃዮችን መንግሥት አቋቁሞ ለመመለስ ፍላጎት እንዳለው እና ከኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር ያለውን ችግር በጋራ ተቋቁመው እንዲኖሩ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡

አምስት ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ያሉት አማራ ክልል ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱ ከቆየችበት ጦርነት፣ የኮቪድ 19 ችግር እና አሁን በሚታየው ችግር ታልፎ እየተሠራ ያለው የመንገድ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች በቀላሉ የሚታዩ አለመኾናቸውን አስረድተዋል፡፡

16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰው የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ እንዲኾን የማድረግ ሥራ እና የትም የማይገኘው የጎርጎራ ልማት ሥራ በቀላሉ የሚታይ የልማት ሥራ አለመኾኑን ተናግረዋል፡፡
ሥራዎቹ እንዲጠናቀቁም በጥብቅ የሚከታተሉት እንደኾነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ የተሠሩ ሥራዎችን ማድነቅ ቱሪስት ወደ አካባቢው እንዲመጣ ለማድረግ እንደሚያግዝም ነው ያብራሩት፡፡

በቴሌኮምኒኬሽን ከ100 በላይ ቀበሌዎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ መደረጉን እና ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ ፋይበር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡ መብራት አግኝቶ የማያውቅ 131 ቀበሌ ማግኘቱንም ነው ያስረዱት፡፡

የተሠራው ሥራ እንዳለ ኾኖ አማራ ክልል ካለው ሁኔታ አኳያ እንደማይበቃም ነው ያብራሩት፡፡ የምኒሊክ ቤተመንግሥት ሲሠራ ፒኮክን ጨምሮ ከውስጥ የሚገኙትን አውጥቶ በሚታይ መንገድ አሳምሮ ለመሥራት የተሞከረ እንጅ አዲስ የተጨመረ ሃሳብ እንደሌለው ነው ያነሱት፡፡

የአማራ ሕዝብ ጀግና የኾነ ሕዝብ በመኾኑ አሁንም በጋራ ሠርቶ ጀግና መኾን እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡ የማዳበሪያ ችግሩ የነበረው በዓለም አቀፍ ችግር መኾኑን ገልጸው ዘንድሮም ቀድሞ ባይሠራ አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ችግር ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ግን ዘላቂው መፍትሔ በሀገር ውስጥ ለማምረት መሞከር እንደኾነ አብራርተዋል፡፡

መንግሥት የሚፈልገው ለሀገሩ ከልቡ ያለ አድሎ የሚሠራ በመኾኑ ይህን ለማድረግ ዝግጁ ለኾነ ሁሉ መንግሥት በሩ ክፍት መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ነገሮችን በአፈሙዝ እና በጉልበት ለማድረግ የሚሞከረው አካሄድ ግን ትክክል አለመኾኑን እና እንደማይሳካ ነው ያስረዱት፡፡ በሰላም ገብቶ የሚሠራ ካለ እንዲመለስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሚካስም ካለ ተክሶ ሰላም እንዲወርድ እና ሥልጣንን በካርድ ማድረግ የመንግሥት አቋም እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከኢትዮጵያ ጋር ለተፈራረመችው ሥምምነት ተፈጻሚነት ቁርጠኛ ኾና እየሠራች መኾኑን ሶማሊላንድ አስታወቀች፡፡
Next articleበአማራ ክልል ወደ ውጭ ከተላከው የእንስሳት ሃብት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱ ተገለጸ።