
ባሕር ዳር: የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለክልል ምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው። ርእሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት በግማሽ ዓመቱ ጠቅላላ የቱሪስት ፍስሰትን 5 ሚሊዮን 884 ሺህ 816 ለማድረስ ታቅዶ ነበር።
ክልሉ የጸጥታ ችግር ገጥሞት የነበረ ቢኾንም በግማሽ ዓመቱ 4 ሚሊዮን 106 ሺህ 512 ቱሪስቶች ክልሉን ጎብኝተዋል ነው ያሉት። አፈጻጸም ከስድስት ወራቱ አኳያ ሲሰላ 69 ነጥብ 8 በመቶ እና ከዓመቱ ደግሞ 57 ነጥብ 6 በመቶ ይኾናል።
በዚህ የቱሪስት እንቅስቃሴ ከሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እና ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች ደግሞ 41 ሚሊዮን 618 ሺህ ብር ተገኝቷል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ በሪፖርታቸው።
የቱሪዝም ዘርፍ በባህሪው የሰላም ዋስትናን የሚፈልግ መኾኑን ጠቁመው የተፈጠረው ግጭት በርካታ የቱሪዝም ተግባራትን በታቀደው ልክ ለመፈጸም እንቅፋት ኾኖ ቆይቷል ብለዋል።
የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በፍጥነት እና በዘላቂነት በመፍታት የቱሪዝም ዘርፉን ገቢ ማሳደግ፤ ሕዝቡንም ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ሲሉ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!