
ባሕር ዳር: የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአፍሪካ የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ገለጸ።
የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በአፍሪካ በተለይም ከሰሀራ በታች በሚገኘው የአህጉሪቱ ቀጣና በዓለም የትምህርት ተደራሽነት ካልተረጋገጠበት አካባቢ ቀዳሚ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የትምህርት ረዳት ዳይሬክተር ጄኔራል ቲፋኒያ ጄኒኒ የአፍሪካን እድገት ለማረጋገጥ ትምህርት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ አሁንም በርካታ ታዳጊ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን እና የትምህርት ጥራት ጉዳይም አሁንም ብዙ ጥያቄ የሚነሳበት መኾኑን ነው ለኢዜአ ያስረዱት።
ይህም በአህጉሪቱ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸው በአህጉሪቱ በትምህርት ዘርፉ ብዙ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በአህጉሪቷ ቀጣይነት ያለው ልማት እና እድገት ለማረጋገጥ ዘርፉ በሚጠበቀው ልክ ሚናውን እንዲወጣ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡ ዩኔስኮም በአህጉሪቱ በዘርፉ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ያጠናክራል ብለዋል።
ዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚፈልግ መኾኑን ጠቅሰው የአፍሪካ ኅብረት ኀላፊነቱን በመውሰድ ለዘርፉ የሃብት ማሰባሰብ ሥራ በስፋት መሥራት እንደሚገባው ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!