
ባሕር ዳር: የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ2016 በጀት ዓመት በሦስት ዙር የመስኖ ልማት 41 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የመስኖ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ተናግረዋል።
በመስኖ ዘርፍ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። በበጀት ዓመቱ በነባር እና በአዲስ ከ333 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ በስድስት ወራት ውስጥ 127 ሺህ 971 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን ጠቁመዋል። ይህም የግማሽ ዓመት አፈጻጸሙ 38 ነጥብ 4 በመቶ መኾኑን ያሳያል።
ከመስኖ ልማት ሥራዎች ውስጥ ወሳኙ የስንዴ ልማት መኾኑንም ጠቁመዋል። በበጀት ዓመቱ 250 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ በሩብ ዓመቱ 132 ሺህ 423 ሄክታር መሬት ለተይቶ 68 ሺህ 563 ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል ብለዋል። ለዚህም 88 ሺህ 269 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 85 ሺህ 686 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ጠንካራ የመስኖ እንቅስቃሴ በማድረግ ተጨማሪ ሥራዎችን ለማከናወን ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ስለመኾኑም ርእሰ መሥተዳድሩ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!