“በአማራ ክልል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት የክልሉን ሕዝብ ከከፍታው ለማውረድ የተደረገ ከንቱ እና አስነዋሪ ሙከራ ነበር” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

35

ባሕር ዳር: የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። በጉባኤ የመጀመሪያ ቀን የጥዋት መርሐ ግብር ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን መንግሥት የ2016 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤት አባላት እያቀረቡ ነው። ርእሰ መሥተዳድሩ ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ የተሠሩ ሥራዎችን በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

ግጭቱ የተያዙ የልማት ሥራዎችን ያደናቀፈ፣ የንብረት ውድመትን ያስከተለ፣ የሰዎችን ሕይወትም የቀጠፈ እንደነበር ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ከመላ ሰላም ወዳዱ የክልሉ ሕዝብ እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር ክልሉን ወደተሟላ ሰላም ለመመለስ ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

የክልሉን የሰላም እጦት ለመመለስ በተሠራው ጠንካራ ሥራ የታቀደውን ሁሉ ሁከት እና ብጥብጥ ማክሸፍ መቻሉን ተናግረዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ ክልሉ ከሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ገና ሳያገግም ሌላ ግጭት መፈጠሩ የክልሉን ሕዝብ ሌላ ዋጋ ያስከፈለ ነበር ሲሉም ተናግረዋል።

“ተፈጥሮ የነበረው ግጭት የክልሉን ሕዝብ ከከፍታው ለማውረድ የተደረገ ከንቱ እና አስነዋሪ ሙከራ ነበር” ሲሉም አስገንዝበዋል። የሰላም እና የይቅርታን ጥሪ ወደ ጎን በመተው ለግጭት መነሳት ለዘመናት የውስጥ ሰላሙን አስጠብቆ የኖረውን የአማራን ሕዝብ የማይመጥን ስለመኾኑም ተናግረዋል። ሰላምን የመረጡ አካላት ጥሪውን ተቀብለው የተሐድሶ ሥልጠና ተሰጥተዋል፤ አሁንም ድረስ እየተመለሱ ሥልጠናውን የሚወስዱም አሉ ብለዋል።

የክልሉ የሰላም እጦት የከፋ ደረጃ ላይ በደረሰ ጊዜ በክልሉ ጥያቄ መሰረት የፌዴራል መንግሥት ባደረገው የሕግ ማስከበር ሥራ በሕዝብ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በወሳኝነት መከላከል ስለመቻሉም ገልጸዋል።

የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ የበለጠ ለማጠናከርም ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ለሚገኙ የፀጥታ መሪዎች እና አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መንግሥት የክልሉን ሰላም ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ወሳኝ ደረጃ ላይ ይገኛል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleበአማራ ክልል 41 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የመስኖ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።