
ፍኖተ ሰላም፡ የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የገቡ የቀድሞው የአማራ ልዩ ኀይል አባለት የተሀድሶ ሥልጠና ሲከታተሉ ቆይተው ተመርቀዋል። ቀደም ሲል ተበትነው የነበሩ የቀድም የአማራ ልዩ ኃይል አባለት ናቸው የተሀድሶ ሥልጠና ወስደው የተመረቁት።
የክልሉን ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ተመራቂወች ተናግረዋል። ክልሉ ከገባበት የፀጥታ ችግር እንዲወጣም ከክልል የፀጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።
የነበሩበት አካሄድ የክልሉን ሕዝብ የማይጠቅም መኾኑን በመረዳት ወደ ሰላም ጥሪው እንደተቀላቀሉም የተሀድሶ ሥልጠና ወስደው የተመረቁት የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባለት ገልፀዋል።
የወሰዱት የተሀድሶ ሥልጠናም የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የአቅም እና የሥነ ልቦና ዝግጁነትን እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን ሠልጣኝ የፓሊስ አባላት ለሕግ እና ሥርዓት ተገዥ በመሆን፣ ታማኝ ገልተኛ እና ቁርጠኛ በመኾን ኀላፊነታችሁን እንድትወጡ ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው፤ ተመራቂወች የክልሉን ሕዝብና መንግሥት በሚገባ በማገልገል የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ ወደነበረበት ለመመለስ በወሰዳችሁት ሥልጠና መሰረት ኀላፊነታችሁን እንድትወጡ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርአቱ የተገኙት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የችግር መፋቻቸውን የኀይል አማራጭ ባደረጉ ኀይሎች የክልሉ ሕዝብ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየተዳረገ ነው ብለዋል። ተመራቂወች ለሕዝብ ሰላም መረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተልእኳችሁን እንድትወጡ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል። መንግሥት የክልሉን ሰላም ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ወሳኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም ርእሰ መሥተዳደሩ ገልፀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!