“የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ማቅረብ ከማምረትም በላይ የህልውና ጉዳይ ነው” ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)

22

ባሕር ዳር: የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከክልሉ አልፎ በሀገራዊ ምርት እና ምርታማነት ላይ የጎላ ሚና እና ተፅዕኖ ያለው የአማራ ክልል የግብርና ሥራ ዘንድሮ ዘርፈ ብዙ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች እየፈተኑት ነው፡፡ በክልሉ ለወራት የዘለቀው የሰላም መደፍረስ ችግር በግብርና ሥራው ላይ ያሳረፈው ሰው ሰራሽ አሉታዊ ተፅዕኖ ከባድ የሚባል ነበር፡፡

የክረምቱ ዝናብ ቀድሞ መግባት እና ፈጥኖ መውጣት የፈጠረው ችግር እንዳለ ኾኖ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ግብርናውን በእጅጉ ፈትኖታል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የግሪሳ ወፍ እና ሌሎች ተያያዥ ተፈጥሯዊ ችግሮች ከሰው ሰራሽ ችግሮች ጋር ተደማምረው የክልሉ የግብርና ሥራ ከማምረትም በላይ የህልውና ጉዳይ እንዲኾን አድርጎታል፡፡

ባለፈው ዓመት በክልሉ የተፈጠረው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ከግብርና ሥራው ችግርነት አልፎ ሌላ የመልካም አሥተዳደር መዘዝ ይዞ እንደመጣም ይነገራል፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ እና የፌደራል መንግሥት ባለድርሻ አካላት ባለፈው ዓመት በክልሉ ተፈጥሮ ከነበረው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ላይ ትምህርት ወስደው በ2016/17 የምርት ዓመት ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር የማዳበሪያ ግዥ ውል ቀድሞ እንዲፈጸም ተደርጓል፡፡

በአማራ ክልል ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልገው 8 ሚሊየን 57 ሺህ 900 ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ ቀድሞ መፈጸሙን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) ነግረውናል፡፡ ከጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምሮም ከወደብ ወደ ማዕከል የአፈር ማዳበሪያውን የማጓጓዝ ሥራው ተጀምሯል ብለዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ በበቂ መጠን እና በወቅቱ አለመቅረቡ የፈጠረውን ስብራት ወስደን ዘንድሮ በልዩ ትኩረት ግዥ ቢፈጸምም በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሌላ መሰናክል ኾኗል ነው ያሉት ዶክተር ድረስ፡፡ ከወደብ እስከ ክዘና ማዕከላት ድረስ ያለው የደርሶ መልስ ጉዞ ከ15 ቀናት በላይ መብለጥ ባይኖርበትም በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት እስከ 45 ቀናት ድረስ ወስዶ እንደነበርም አንስተዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ በምርት ዘመኑ በክልሉ ከ160 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅዶ እየሠራ ቢኾንም በተከሰተው ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት በቅድመ ምርት ግምገማ 145 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብቻ ሊገኝ እንደሚችል መረጃዎች ያመላክታሉ ተብሏል፡፡ ቅድመ ምርት ግምገማው ባለፈው ዓመት ከሰበሰበው 140 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተሻለ ምርት እንደሚኖር ያመላክታል፡፡

ነገር ግን ዶክተር ድረስ እንደሚሉት ካለፈው ዓመት የተሻለ ምርት የሚኖረው ምርትና ምርታማነት ጨምሮ ሳይኾን በተያዘው በጀት ዓመት ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ ጭማሬ መሬት ስለታረሰ ነው ይላሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ 29 ኩንታል ምርት የተገኘው ሲኾን በዘንድሮው የምርት ዘመን በአንድ ኩንታል ቀንሶ 28 ኩንታል ከሄክታር እንደተገኘ መረጃው ያመላክታል ነው ያሉት፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ግብርናን ከማምረትም በላይ ሁለት ታላላቅ ሽግግሮችን እንዲያመጣ ይፈልጋል ይላሉ ዶክተር ድረስ፡፡ የመጀመሪያው ሽግግር ለአርሶ አደሩ መድረስ ያለበትን የግብርና ግብዓት በሚፈለገው መጠን እና ወቅት በልዩ ትኩረት አድርሶ ምርት እና ምርታማነት ላይ የጎላ ልዩነት ማምጣት ነው ተብሏል፡፡ ሌላው የክልሉ ግብርና ሽግግር ደግሞ የአርሶ አደሩን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲሸጋገር ማገዝ ነው ተብሏል፡፡

አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደብ ላይ ይገኛል ያሉት ኀላፊው በመጻዒዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ከወደብ ወደ ክዘና ማዕከላት በማድረስ ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ወቅቱ የሚጠይቀው የአርበኝነት ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ ተግባር ሥኬትም በተለይም አራት አካላት ሚናቸው የጎላ እንደኾነ ዶክተር ድረስ አንስተዋል፡፡

ማኅበረሰቡ በተለይም አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያው በተቀመጠለት ጊዜ በበቂ መጠን እንዲደርስ የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ወደ ክልሉ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ ከወደብ ወደ ክዘና ማዕከል የሚያደርሱ 14 የትራንስፖርት ድርጅቶች አሉ ያሉት ዶክተር ድረስ ከንግድ በላይ የኾኑ ማኅበራዊ ኅላፊነት እንዳለባቸው ተረድተው ዘመኑ የሚጠይቀውን የአርበኝነት ተግባር መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች የአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ ሥራው በተሳካ መንገድ እንዲፈጸም እየሠሩ ነው ያሉት ኀላፊው ግብርና እና ባለድርሻ አካላት ኮሚቴ አቋቁመው ሥራውን ቀን ከሌት እየተከታተሉ እንደኾነም አንስተዋል፡፡ ለክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት በዚህ ወቅት የአፈር ማዳበሪያን ለተጠቃሚዎች በወቅቱ ከማድረስ በላይ የሚኾን ተግባር የላቸውም ያሉት ዶክተር ድረስ ምክንያቱም “የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ማቅረብ ከማምረትም በላይ የህልውና ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡

በምዕራብ አማራ ቀጣና የሚስተዋለውን ዝቅተኛ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በቀጣይ ቀናት በማድረስ ምርታማነትን ለማሳደግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ዶክተር ድረስ አሳስበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መሪን የሚወልደው እና የሚያጀግነው ሕዝብ ነው” ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next article“መንግሥት የክልሉን ሰላም ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ወሳኝ ደረጃ ላይ ይገኛል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ