“መሪን የሚወልደው እና የሚያጀግነው ሕዝብ ነው” ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

28

ባሕር ዳር: የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ከየካቲት 13 እስከ የካቲት 15/2016 ዓ.ም የሚቆየውን 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ አማራ ክልል ካጋጠመው የፀጥታ ችግር ተላቅቆ አንጻራዊ ሰላም እንዲያገኝ ትብብር ላደረጉ አካላት እና ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የፀጥታ አካላት እና ሰላም ወዳዱ የአማራ ክልል ሕዝብ አሁን ለተገኘው ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል። የተገኘው አንጻራዊ ሰላም አስተማማኝ እና ዘላቂ እንዲኾን አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች ሥለመኖራቸውም ጠቁመዋል።

ዋና አፈ ጉባኤዋ አማራ ክልል ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና አገልጋይ የኾኑ አመራሮች እንዲኖሩት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። ለዚህም በክልሉ አዳዲስ እና ጠንካራ አመራሮችን የማዋቀር ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።

ዋና አፈ ጉባኤዋ “መሪን የሚወልደው እና የሚያጀግነው ሕዝብ ነው” ሲሉም በአንክሮ ተናግረዋል። መሪን መውለድ፣ ማጀገን፣ ሲያጠፋም መምከር እና እድል በመስጠት ማስተማር የሕዝብ ኀላፊነት ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። በመኾኑም የክልሉ ሕዝብ ከመሪዎቹ ጎን በመቆም እና በመደገፍ ለልማት መሥራት ይገባዋል ብለዋል።

ሕዝብ የወለዳቸውን መሪዎች መደገፍ፣ ማጀገን እና ማብቃት ካልተቻለ በልማት ተጠቃሚ እና ተወዳዳሪ ሕዝብ መፍጠር አይቻልም ሲሉም ተናግረዋል ዋና አፈ ጉባኤዋ በመክፈቻ ንግግራቸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጋር የሚያገናኘው የተከዜ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ተጀመረ።
Next article“የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ማቅረብ ከማምረትም በላይ የህልውና ጉዳይ ነው” ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)