
ባሕር ዳር፡ የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለአራት ዓመታት ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ የቆው የተከዜ ወንዝ ድልድይ ከ256 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው መጀመሩ ተገለጸ፡፡
ግንባታው በሦስት ወራት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግ መገለጹን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
አጠቃላይ የድልድዩ ርዝመት ከ155 ሜትር በላይ ነው። ከዚህ ውስጥ በመካከል ከ60 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ተገጣጣሚ የብረት ድልድይን መሠረት አድርጎ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ነው ተብሏል፡፡
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የዝቋላ እና ሰሀላ-ሰየምት ወረዳዎች መካከል የሚገኘው ድልድይ ብሔረሰብ አስተዳደሩን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጋር የሚያገናኝ ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቀደም ሲል የነበረው ተገጣጣሚ የብረት ድልድይ በደለል በመዋጡና በጎርፍ በመወሰዱ ምክንያት ላለፉት 4 ዓመታት አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱም ተጠቁሟል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!