መረዳዳት

66

ባሕር ዳር: የካቲት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለወትሮው ያለው ለሌለው፣ ያገኘው ላጣው ለነጣው፣ ያለችውን አካፍሎ መብላት፣ አብሮ መኖር፣ ለቸገረው ማበደር፣ ሲቸግር መበደር እና በወቅቱ አመስግኖ መመለስ አብሮ የኖረ ትልቁ እሴታችን ነው። መረዳዳት የኢትዮጵያውያን ነባር እሴት ነው፡፡

በመረዳዳት በርካቶች ክፉ ቀንን አልፈውበታል፤ መከራቸው ተገፍፎ ሰላማቸው ታውጇል፤ ርሃባቸው ተወግዶ ምግብ በልተዋል፤ የዘመመው ጎጇቸው ተቃንቶ ዳግም ሰው ተብለዋል፤ በህመም የጠወለገው ሰውነታቸው ለምልሞ ለዓይን ሙሉ ኾነዋል። የታረዘው ገላቸው ሙቀት ጎብኝቶታል፡፡ ይህ ሁሉ ከልብ የመነጨው መረዳዳት እና መደጋገፍ የወለደው ሃሴት ነው። ዛሬ ዛሬ መረዳዳት የሚባለው እሴታችን እየደበዘዘ መጥቶ መትረፍ የምትችል ሕይዎት ስታልፍ፤ መሻገር የሚቻል ፈተና ሲያሰናክል እያስተዋልን ነው።

ወርቃማው የኢትዮጵያዊያን ነባር እሴት ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ባይባልም ችግር ግን ገጥሞታል። ለዚህም ማሳያው በዓላት በመጡ ቁጥር አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ ተብሎ የሚደረገው ሽር ጉድ፣ በአንዳንድ በጎ አድራጎት ማኅበራት ለተሰበሰቡ አቅመ ደካሞች በቋሚነት የሚደረገው ድጋፍ እና ሌሎች ድጋፎች ሙሉ በሙሉ ላለመጥፋቱ ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ተግባራት መኖራቸው ግን መረዳዳት አለ እየተረዳዳን ነው፣ ችግሮችን በመተጋገዝ እያለፍን ነው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም።

ምክንያቱ ደግሞ ይህ ድጋፍ ወይም እርዳታ ወቅታዊ ወይም ሰሞነኛ ነው። መረዳዳት ከአስተሳሰብ የሚጀምር ቢኾንም ምግብ፣ አልባሳት፣ የህክምና ወጭ፣ ለሥራ መጀመሪያ የሚኾን ገንዘብ፣ የሞራል ድጋፍ እና ሌሎች መገለጫዎች አሉት።

ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ መረዳዳትን አጥብቀን እንድንይዝ የሚያስገድደን ቢኾንም እኛ ግን ዘንግተነው በዓላት ሲመጡ ብቻ ምግብ እና አልባሳት ለመስጠት የምናደርገው ሩጫ ጉዳዩን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባዋል።

ጉዳዩ ትኩረት የሚሻ በመኾኑ አካባቢን ማየት እና መገንዘብ ችግሩን ለመፍታት የመጀመሪያው ርምጃ ነው።
በርካቶች በርሃብ ጠኔ ውስጥ ናቸው። ርሃቡን መቋቋም አቅቷቸው በየጎዳናው ዳር ወድቀው የሚታዩ ሰዎች ቁጥር በርካታ ነው። በሰላሙ ጊዜ ተሯሩጠው ያገኙትን ሠርተው የቤታቸውን ገመና ሸፍነው የሚያድሩ የጉልበት ሠራተኞች ዛሬ መንቀሳቀሻ በጠፋበት በዚህ ሰዓት ለችግር ተዳርገዋል።

በሥግብግ እና ሕገ ወጥ ነጋዴዎች በየጊዜው የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ እንደምንም ተሯሩጠው ሰርተው በሚያገኙ ሰዎች ድካም ላይ ውኃ እየቸለሰ ተስፋ አስቆራጭ ኾኗል። ብዙዎች ለችግር እጅ ላለመሥጠት ልጅ አዝለው በቀን ሥራ ደፋ ቀና ይላሉ። ኑሮ ፈተና ውሎ ማደር ግብግብ የኾነባቸው በርካቶች ናቸው።

በአካባቢያችሁ ከሚኖሩ ሰዎች ምን ያህሎቹ በአግባቡ ምግብ እንደሚያገኙ ራሳችሁን ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ። ምን ያህሎቹ መታከሚያ አጥተው የሞታቸውን ቀን አልጋቸው ላይ ኾነው እየተጠባበቁ እንደሚኖሩስ? ምን ያክሎቹ ሀገር የሚጠቅም እውቀት ይዘው ራሳቸውን ለመመገብ የቀን ሥራ እንኳን አጥተው በርሃብ ጠኔ ውስጥ እንደኾኑስ? ሥራ የሚጀምሩበት ጥቂት ገንዘብ አጥተው እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡ ብዙ ሰዎች እንዳሉስ?

አንድ በቅርብ የምታውቁት ሰው መንገድ ላይ ተቀምጦ ሲለምን ብታገኙት የእናንተ ምላሽ ምን ሊኾን ይችላል? እንዳያያችሁ መደበቅ? ደግሞ ወደዚህ ሥራ ገባህ ብሎ ማሽሟጠጥ፣ ይህ ሰው “ሰላይ ነው” ብሎ መጠርጠር? አሊያም ድሮም ሌላ ቦታ ይለምን ነበር ማለት ነው ብሎ ማሰብ በብዙዎቻችን አዕምሮ ውስጥ ከሚመላለሱ ጥያቄዎች ውስጥ ጥቂቶች ናቸው።
ምን ያህሎቻችን ነን የገጠመውን ችግር መጠየቅ የምንችል፣ ጠይቀንስ ሰውየው ከገባበት ችግር ውስጥ ለማውጣት ጥረት የምናደርግ።

የታመመን ለመርዳት እና ለማሳከም ያለን ፍላጎትስ ምን ያክል ነው? አንዳንድ እድሮች ሰው ሲሞት ከመቅበር ወጥተው ሰውየው ወይም ሴትየዋ ታክማ ከህመማቸው እንዲፈወሱ የማድረግ ባሕላቸው ይበል የሚያሰኝ ቢኾንም አንዳንድ እድሮች ግን ዛሬም ትኩረታቸው ሲሞቱ ቀብር ማስፈጸም ብቻ ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡

እድሮች ከአባሎቻቸው ከሚሰበስቡት ገንዘብ ባለፈ አባሎቻቸው በምን ችግር ውስጥ እንዳሉ ቃኝተው ያውቃሉ? በገንዘብ እጦት በችግር የሚርመጠመጡ አባሎቻቸው ነገ ብሞት የሚቀብረኝ የለም በሚል ከልጆቻቸው ጉሮሮ ነጥቀው እንደሚጥሉስ ጥናት አድርገዋል? ከቀብር በፊት ሴትየዋ ወይም ሰውየው እና ልጆቻቸው አይቀድሙም ነበር። ሕግ እና ደንብ አዘጋጅተው ከተሰበሰበው ገንዘብ ተበድረው እንዲሠሩ እና እንዲመልሱ ማድረግ የቻለ እና እያቋቋሙ ያሉ ምን ያክሎቹ ይኾኑ?

ዛሬ መተማመን ጠፍቶ አበዳሪ በጠፋበት ወቀት ለአባሎቻቸው ማበደር፣ የታመመን ማሳከም ቢችሉ ተሰብስበው አናታችን ላይ ከተቆለሉት ችግሮቻችን ጥቂቶችን ቀረፉልን ማለት አይደለም።

መቼ ነው ሰው የመጨረሻ አማራጩ ላይ ደርሶ “ኢትዮጵያ ውስጥ መታከም አይችልም” ተብሎ ጎዳና ላይ ሲወጣ ብቻ ለመርዳት እጃችንን መዘርጋት የምናቆም? ሰዎች ህመሙ የሚጀምራቸው ቀድሞ ነው። መታከሚያ ሥለሌላቸው ህመሙ ጠንቶ እስኪጥላቸው ድረስ የአቅማቸውን ብቻ ሲታከሙ ቆይተው አንድ ቀን ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ አደገኛ ሁኔታ ላይ ሲደርስ ኮሚሽን ሰብሳቢዎች መኪና ላይ ሞንታርቦ ጠምደው ለልመና ይዘዋት ወይም ይዘውት ሲወጡ መመልከት የተለመደ ተግባር እየኾነ መጥቷል። ለእኔ ይህ ትልቁ ትዝብቴ ነው እናንተስ? ገንዘብ እያላችሁ በምን አገባኝ ስሜት ብዙ የሀገር ባለውለታዎች “ቢታከሙ ኖሮ መኖር ይችሉ ነበር” እየተባሉ ላይመለሱ ሲያሸልቡ ያየናቸው።

ሌላው የትዝብቴ መነሻ በርካቶችን በማግባባት ሌሎችን እረድተው የሥጋም የነፍስም እርካታ እንዲያገኙ የሚያደርጉ ደጋግ ልብ ያላቸው ወገኖች ባሉበት ሀገር ጥቂቶች እነእከሌን ልንረዳ ነው በሚል ድጋፍ በማሰባሰብ አምስት ኪሎ መኮረኒ ሠጥተው ፎቶ የሚነሱስ አላጋጠማችሁም። የራስን ኪስ ለማድለብ የሌሎችን ኪስ ማጎድጎድ የሚያስከፍለው ዋጋ ትልቅ መኾኑን ልብ ሳይሉት ቀርተው ይኾን። ነገ እነዚህ ደጋግ ልብ ያላቸው ሰዎች ጉዳዩን የተረዱት ዕለት ምን ሊሰማቸው ይችል ይኾን?

አንዳንድ ሰዎች ከሥራቸው ብዛት የተነሳ ለሌሎች ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ላያስታውሱ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ሌሎች ያደረጉትን ድጋፍ ሰምተው እኔስ ምን ባደርግ ይሻለኛል ብለው ራሳቸውን እንዲጠይቁ እና ወደ ተግባር እንዲገቡ ለማድረግ የሚዲያዎች ሚና ከፍተኛ ቢኾንም ሳይሠጡ በሚዲያ ለማስነገር የሚጣደፉ እንዳሉስ ምን ያህሎች ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ።

ለነገሩ “ቀኝህ ሲሠጥ ግራህ አይይ” የሚለው የመጽሐፍ ቃል የተዘነጋ እስኪመስል ድረስ ፎቶ ተነስቶ መለጠፍ፣ ከኔ ወዲያ ላሳር ብሎ ሌሎችን ማጣጣል፣ የተረጅውን የዓመት ቀለብ ያቀረብን እንዳያስመስለን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች እንደቸገረን ሳንነግራቸው ችግራችንን ተረድተው ሊያግዙን ሲሞክሩ ይስተዋላል። ጥቂቶች ደግሞ ችግር እንደገጠመን ሲያውቁ ከችግሩ የምንወጣበትን ሳይኾን ችግሩ የሚባባስበትን መንገድ ሲተልሙ ይታያሉ።

አንድ ሰው የሚበላው አጥቶ መለመን እንደሌለበት አምኖ ግን ከምሞት ለምኜ በልቼ ነፍሴን ላሳድራት ብሎ ከራሱ ጋር ተሟግቶ ርሀቡ ሞራሉን አሸንፎት ለልመና እጁን ቢዘረጋ ምን ያህሎቻችን ርቦት ነው፣ አጥቶ ነው ብለን በቀና አስተሳሰብ ተቀብለነው ያለንን የምናካፍል? እኔን ጨምሮ የሚቀናን “ሰርቶ አይበላም” የሚለው ሃሳብ ቀድሞ አፋችን ላይ ድቅን ይልና ሃሳቡን ሳናዳምጠው ፊት ነስተን ከፊታችን እናባርረዋለን። አንዳንድ ጊዜ ሰበብ አድርጎ ሊዘርፈኝ ነው የሚል ሥም በመስጠት ለዱላ የምንጋበዝ እንደማንጠፋ ሁሉ፡፡ ይህን ሥልት ተጠቅመውም ለዘረፋ የተሰማሩ የሉም ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡

በጉዳዩ ላይ ሥናዎራ አንድ አባት ትዝብቴን አጠናከሩልኝ፡፡ ከዘመናት በፊት አንድ ሰው በችግር ምክንያት ጉዳት እንዳያገኘው እንኳንስ ከቅርብ ያለ ሰው ከሩቅ ሀገር መጥቶ ያግዘው፣ ከችግሩ የሚወጣበትን መንገድ ያመቻች ነበር፡፡ ወንድሜ እኔ እያለሁ አንተ አትቸገርም ይባባሉ እንደ ነበር አጫውተውኛል፡፡ ርሃብ እማ አይታሰብም እንኳንስ ጎረቤቱ ላለው ይቅርና የእግዚአብሔር እንግዳ ጠይቆ ለገባ እንኳን ጦሙን አያድርም ብለዋል፡፡

በትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተከሰተው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሴት የመንግሥት ሠራተኞች ተናገሩ።
Next articleየቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት እየተመረቁ ነው።