ለዘላቂ ሰላም መስፈን የምሁራን እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተገለጸ።

47

ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የምሁራን እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ተገለጸ። “ለዘላቂ ሰላም እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የምሁራን ሚና” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ሀገራዊ ውይይት ተካሄዷል።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ አቶ የሻምበል ክንዴ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሑፍ ኢትዮጵያ እያጣች ያለው ሰላም የሚመለሰው በጦርነት ሳይኾን በሰላማዊ ውይይት ብቻ ነው ብለዋል።

ምሁራን ከመደበኛው መማር ማስተማር ባለፈ ለግጭት የሚዳርጉ የፖሊሲ ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። አቶ የሻምበል ሁሉም አካል የራሱን ሃሳብ ብቻ “የኔ ይበልጣል” ከሚል የተዛባ አመለካከት ወጥቶ በሕዝባዊ ውይይት የዳበረ ሃሳብ አክብሮ እንዲቀበል እና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅ የወቅቱ የዜግነት ግዴታ ነው ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልዓከ ብርሃን ፍስሓ ጥላሁን የታጣውን ሰላም ለማስተካከል አባቶች ለሀገር መሪዎች የሠላም አቅጣጫን እና ስልታዊ ጥበብን ማመላከት አለባቸው ብለዋል።

የሰላም ውሉ በጠፋበት ወቅት የተቋጠረው መጥፎ ትርክት እንዲፈታም የሃይማኖት አባቶች በየቤተ እምነታቸው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የአማራ ክልል ሽምግልና ማኀበር ፕሬዝዳንት ሊቀ ኀሩያን በላይ መኮንን “ሰማይ ተቀደደ ቢለው፤ ሽማግሌ ይስፋው” ተባለ እንዲሉ የሰላም እጦቱን ለማስወገድ የሀገር ሽማግሌዎች በፖለቲካ ሳይጠለፉ ስለ ሰላም በመምከር፣ በመገሰጽ ፣ ቁርሾ ሲከሰትም በየውይይቱ ሰላም አምጭ ሃሳብ በማዋጣት ለሰላማዊ የሀገረ መንግሥት ግንባታ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ፖለቲከኞችም ልበ ቀና ኾነው የምሁራኑን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ምክረ ሃሳብ በማድመጥ ወደ ሰላም ሊመመጡ ይገባቸዋል ነው ያሉት ። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ለዓለም ሕዝብ ኹሉ የሰላም እና የነጻነት ቀንዲል ነበረች ሲሉ አስታውሰዋል። አሁን ሀገራችን የገጠማትን ስብራት እና ክፍተት ለማስተካከል በመወያየት መፍትሄ መፈለግ ከምሁራን እና ከአባቶች የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው ብለዋል።

ዶክተር ፍሬው የሥልጣኔ ማማ ላይ የነበሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በታሪክ ከፍ እና ዝቅ በማለት ሲወድቁ ታይተዋል ሲሉ ገልጸዋል። ነገር ግን አብዛኞቹ ሀገራት ከወደቁበት ተነስተዋል። ሌሎቹ የተነሱበትን ጥበብም እኛ በውይይት አዳብረን ወደ ሀገራችን ማምጣት እና የተለያዩ ባለድርሻ ወገኖችም ለሠላም የሚሠሩበትን መንገድ ማሳየት ከውይይቱ የሚጠበቅ ጭብጥ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- በሙሉጌታ ሙጨ

Previous article“በግብርናው ዘርፍ ተቋማዊ ሽግግር ማምጣት የሚያስችል የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ነው” ድረሥ ሳሕሉ (ዶ.ር)
Next articleከሀሰተኛ መረጃ በመራቅ የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ እንደሚገኙ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶች ተናገሩ።