“በግብርናው ዘርፍ ተቋማዊ ሽግግር ማምጣት የሚያስችል የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ነው” ድረሥ ሳሕሉ (ዶ.ር)

27

ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ልማት አጋር አካላት የመማማሪያ እና የፖሊሲ ውይይት ለአምስተኛ ጊዜ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረሥ ሳሕሉ (ዶ.ር) “የግብርናውን ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የሚያስችል የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ይገኛል” ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ጥናቶች እየተካሄዱ መኾኑን አንስተዋል።

በግብርናው ዘርፍ ተቋማዊ ሽግግር ለማምጣት ከግብርና ተቋም ባለፈ የሁሉንም ድጋፍ እንደሚጠይቅ ያነሱት ኀላፊው የአጋር አካላት የመማማሪያ እና የፖሊሲ የውይይት መድረክ መፈጠሩ ለዚህ ግብዓት እንደሚኾን ገልጸዋል።

የግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አልማዝ ግዜው (ዶ.ር) እንዳሉት በአማራ ክልል ከሚገኙ 374 ፕሮጀክቶች ውስጥ 85 በግብርናው ዘርፍ ላይ እየሠሩ ይገኛሉ። ፕሮጀክቶቹ በተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ፣ በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ እና በሌሎች ዘርፎች በመሰማራት ዘርፉን በማዘመን፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። በክልሉ የ11 ቢሊዮን ብር አገልግሎት በመሥጠት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት። ፕሮጀክቶቹ በድግግሞሽ ለ5 ሚሊዮን ሕዝብ ተደራሽ እያደረጉ መኾኑንም ነው የገለጹት።

ይሁን እንጂ ፕሮጀክቶቹ ከዚህ በፊት በተደራጀ መንገድ ሳይኾን በተናጠል፣ በሚፈልጉት ቦታ እና ሥራ ላይ ይሰማሩ ስለነበር የሚጠበቀው ውጤት እንዳይመጣ አድርጎት ቆይቷል።
ችግሩን ለመቅረፍ የመንግሥት እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የምርምር ተቋማትን፣ የግል ድርጅቶችን ባቀናጀ መልኩ የጋራ ፎረም ተመሥርቶ ላለፉት ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል።

ፎረሙ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመለየት ለማስፋት፣ የፖሊሲ ማዕቀፍ በሚሹ ጉዳዮች እና ስትራቴጂዎች ላይ ውውይት ለማካሄድ እና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ፣ የሃብት እና የሥራ ድግግሞሽን ለመቀነስ ድርሻው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል።

በወርልድ ቪዥን የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አሥተባባሪ ቴዎድሮስ አባተ የመማማሪያ እና የፖሊሲ ውይይት መድረኩ ድርጅቱ እየሠራ ያለውን ሥራ ከማስተዋወቅ ባለፈ ሌሎች ድርጅቶች እና መንግሥት እያከናወናቸው ከሚገኙ ሥራዎች ልምድ ለመቅሰም ማገዙን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት የነበረውን ተናጠላዊ አሠራር በማስቀረት በጋራ መሥራትን ማዳበር ተችሏል ብለዋል። ችግሮችን በጋራ መፍታት እና እርስ በርስ እንዲተዋወቁ እድል መፍጠሩን ነው የገለጹት።

በአማራ ክልል “አክሽን ኤጌነስት ሀንገር” ማናጀር በሪሁን ጎቤ እንዳሉት ደግሞ የጋራ መድረኩ በአንድ አካባቢ ይከማች የነበረውን ሃብት አስቀርቷል። የሚሠሩ ሥራዎችን ሌሎች ድርጅቶች እንዲያውቋቸው አድርጓል። አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማምጣትም አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስታወቀ፡፡
Next articleለዘላቂ ሰላም መስፈን የምሁራን እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተገለጸ።