
ጎንደር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስታውቋል፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ እና ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ተገኝተው የመስኖ ስንዴ ልማቱ ያለበትን ሁኔታ ተመልክተዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያም በዞኑ 17 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ ነው ብለዋል። ለመስኖ ልማት የግብዓት አቅርቦት እና የካናል ማጽዳት ተግባር መከናወኑንም ገልጸዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የገበያ ትስስር በመፍጠር ለጎንደር ከተማ እና ለሌሎችም ወረዳዎች ምርት ሳይባክን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲኾን እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ወዳጀ ባንቴ ወረዳው ለመስኖ ልማት ምቹ መኾኑን አንስተው በወረዳው 3 ሺህ 466 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 2 ሺህ 850 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ያለው የመስኖ ስንዴ ልማት ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ መኾን የሚችል መኾኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ እየተመረተ ያለው የመስኖ ስንዴ ምርት በጎንደር ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለተገነባው ዳቦ ቤት ግብዓት ለማቅረብ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ምርቱን ለዩኔኖች እና ለሸማች ማኅበራት በማቅረብ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንደሚደረጉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!