
እንጅባራ: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤት ሠራተኞች የውይይት መድረክ ”ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ መልእክት በእንጅባራ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የኅብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እና አሁናዊ ክልላዊ ነባራዊ ሁኔታን ለመቀየር በሚደረገው ጥረት የመንግሥት ሠራተኞች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓለሙ ሰውነት ሥልጠናው የመንግሥት ሠራተኞች ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ፀጋዎችን በውል ተረድተው ወደ ሃብት መቀየር እንዲችሉ ግንዛቤ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚስተዋለው ሙስና እና ብልሹ አሠራር ለሀገራዊ ቀውስ መባባስ እንደ ምክንያትነት ያነሱት ኀላፊው የመንግሥት ሠራተኞች ኅብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል የገቡትን ቃል በተግባር ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ትዕግስት መኩሪያ በአንዳንድ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚስተዋለው ብልሹ አሠራር እና የሠራተኞች ስብዕና መጓደል ኅብረተሰቡ በተቋማት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው እያደረገ በመኾኑ ሊታረም እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሠራተኞችን የሥራ ምዘና ሥርዓት ከሚያገኟቸው ጥቅማ ጥቅሞች ጋር በማስተሳሰር እና የማትጊያ ሥርዓት በመዘርጋት የሥራ ተነሳሽነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ኀላፊዋ ተናግረዋል።
የመንግሥት ሠራተኛው ትልቅ የመንግሥት የልማት አቅም ነው፤ መንግሥት ይህንን አቅም በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊዎች ናቸው።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የመንግሥት ሠራተኞችን የሥራ ተነሳሽነት እያዳከመ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ መንግሥት ማስተካከያ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!