
ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ.ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ የቱሪስት መስህቦችን ማልማቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የቱሪስት መስሕቦችን እና መዳረሻዎችን በማልማት ሕዝቡን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በተጓዳኝም ሰላሙ ላይ መሥራትም ለቱሪዝም ዘርፉ ያለውን ፋይዳ አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ(ዶ.ር) መንግሥት ሥራው ችግኝ መትከል፣ ማጽዳት እና ፓርክ መገንባት ብቻ ኾነ የሚሉ ትችቶች እንደሚሰሙ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥሩ ዛፍ፣ ጥሩ አበባ እና ጥሩ መዓዛ የምትመሰለውን ገነትን ለመውረስ የሃይማኖቱን ሕግጋቶች አጥብቆ እንደሚተገብር የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ በምድር ላይ ለሰው ልጅ ምቹ ከባቢ መፍጠር መጠላት እንደሌለበት ገልጸዋል። ቱሪዝምን ከገቢ ማስገኛ ብቻ ሳይኾን የኑሮ ዘይቤ ለመውረስም ጭምር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ታችኛው ቤተ መንግሥት የማልማተቱ ፕሮጀክት 3 ሺህ 400 ሠራተኞችን መያዙን እና አንድነት ፓርክ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ ማስገኘቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርክ መገንባቱ ማማሩ ብቻ ሳይኾን ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ገቢ ለማመንጫት እንደሚያግዝ አመላክተዋል።ስለኾነም ችግኝ መትከሉ እና አካባቢ ማጽዳቱ ብሎም መስሕብ የኾኑ ቦታዎችን ሁሉ ማልማቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!