
ደብረ ታቦር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሰላማቸውን እየጠበቁ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራቸውን እየሠሩ መኾናቸውን በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ እየሠሩ ነው። ለዓመታት በሠሯቸው የተፈጥሮ ሃብት ሥራዎች የተቦረቦሩ አካባቢዎችን ወደ ልምላሜ መመለስ መቻላቸውንም ገልጸዋል። የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ምርትን እየጨመረላቸው እና ለእንስሳት መኖ የተሻለ እየኾነ መምጣቱንም ተናግረዋል።
በፋርጣ ወረዳ ቆለይ ቀበሌ ባስኩራ ተፋሰስ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ሲሠሩ ያገኘናቸው አማረ አድማሴ የተፈጥሮ ሃብት ሥራዎችን በራሳቸው ተነሳሽነት እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ የተፈጥሮ ሃብት እንዳይቋረጥ በሚል ሥራ መጀመራቸውንም ገልጸዋል። አረንጓዴ ልማት ለማልማት የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል። የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ለረጅም ጊዜ ልምድ ያካበቱበት እና ጥቅሙንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረዱት መምጣታቸውንም ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ጥቅም በማስገኘቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ያለ ቀስቃሽ እየተነሳ እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። ሰላማቸውን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በማቀናጀት እየጠበቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የተሻለ ሰላም መኖሩንም ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የቆለይ ቀበሌ ነዋሪዋ ወርቄ አንዳርጌ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ እንደወትሮው ሁሉ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። የአፈር እቀባ በመሥራት አትክልት እየተከሉ ተጠቃሚ እየኾኑ እንደሚገኙም አመላክተዋል። የተፈጥሮ ሃብት ሥራ የአካባቢውን ገጽታ እንደሚቀይርም ተናግረዋል።
ለልማት እንቅፋት የሚኾን የሰላም ችግር እንዳልገጠማቸውም ገልጸዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ለሰላም እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የሰላም እጦት እና ክፉ ሃሳብ ሕዝብ ከመጉዳት የዘለለ ሌላ ጥቅም እንደሌለውም ነው የተናገሩት።
የፋርጣ ወረዳ አሥተዳዳሪ ሙሉ አበጀ በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ በታሰበው ልክ ሳይሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። ልማት ወዳድ የኾነው የአካባቢው ማኅበረሰብ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ወሳኝ መኾኑን በመረዳት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በወረዳው በተለያዩ ቀበሌዎች የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የተፈጥሮ ሃብት ሥራዎችን በሁሉም ቀበሌዎች የማዳረስ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ ለልማት እያሳየው ያለው ቁርጠኝነት እንደሚደነቅም ተናግረዋል። የልማት ሥራቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ በተፈጥሮ ሃብት ሥራ የታወቀ መኾኑንም ተናግረዋል። በተሠራው የልማት ሥራ በርካታ ለውጦች መታየታቸውንም ገልጸዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ በርካታ ጫናዎችን ተቋቁሞ ልማቱን እንደሚሠራም አስታውቀዋል። የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀምም እቅዳቸውን ለማሳካት እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!