
ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ14ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የአማራ ክልል ለቱሪስት ምቹ እንደኾነ ገልጸዋል። የአካባቢውን ባሕል እና መልካምድር ታሳቢ በማድረግ የጎርጎራ ፕሮጀክት መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡
የጎርጎራ ፕሮጀክት በርግጠኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ እና አሁን ባለው መረጃ በአፍሪካ ደረጃ የዚያን ያክል ግዙፍ የኾነ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራ እንደሌለ አብራርተዋል፡፡
በጥራቱም ለትውልድ የሚሸጋገር ፕሮጀክት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ ይህም የኾነው ሕዝቡ የሚፈልገውን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ካለ እሳቤ በመነሳት እንደኾነም ነው የተናገሩት፡፡
ላሊበላን በተመለከተም ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር በመተባበር ራሳቸው ፕሬዚዳንት ማክሮንን በመውሰድ እና በማሳየት የጥገና ሥራው ስለመጀመሩ አስረድተዋል፡፡
የላሊበላ ድንቅ የእጅ ሥራ ሳይበላሽ ለትውልድ እንዲተላለፍ እሳቤ ያደረገ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ተጨማሪ ገቢ ማምጣት እንዲቻል ታሳቢ ያደረገ ተግባር እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
ይህ ሥራም ከቱሪስት መስሕብነት በዘለለ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥር እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡ድንቅ የኾነው የፋሲል ቤተ መንግሥትም ግማሽ አካሉ የፈረሰ በመኾኑ እና ጉዳት ያለበትን ቤተ መንግሥት ነው ስናስጎበኝ የኖርነው ይህ ተገቢ አይደለም በሚል ሰፊ እንቅረስቃሴ ስለማድረጋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ይህን ሥራ ለማከናወንም ከመደመር መጽሐፍ በሚገኝ ሽያጭ ለመሥራት ጥረት ስለመደረጉ እና ከመጽሐፉ የተገኘው ገቢ እስኪደርስ ከሌላ ምንጭ ለመጠቀም ጥረት ቢደረግም በተለያዩ አሉባልታዎች ሥራው እንዳይከናወን እንደተደረገም ነው የተናገሩት፡፡
ፋሲል ላይ የታሰበው ጥገና የሚኒሊክ ቤተ መንግሥት እና የኃይለሥላሴ ቤተ መንግሥት እንደታደሰው አድርጎ በተሻለ ለማደስ ታሳቢ ያደረገ እንደነበርም አስገንዝበዋል፡፡ የጸጥታው ሁኔታ ባያግድ የጣና ሐይቅን ውኃ ከጎንደር ጋር ለማስተሳሰር በርካታ ጥናቶች መደረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!