
ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡ በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ አባላቱ ላነሷቸው ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ወቅታዊ የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት አቋሞች ዙሪያ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሲመልሱ “የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ማዕከሉ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር ነው” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ከምዕራቡ ዓለም ወጥታ ወደ ምሥራቁ ዓለም ለመጠጋነት ነው የሚለው ትችትም የዲፕሎማሲን ጽንሰ ሃሳብ ካለመረዳት የሚመነጭ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው በመሰባሰብ ውስጥ የሚገኘውን ጥቅም ለመጋራት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኢትዮጵያ በላይ ቻይና እና አሜሪካ የጠንከረ ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር አላቸው ነው ያሉት፡፡ በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ በተለይም ለድሃ ሀገራት የማይመች እና የማይጠቅም አሠራር ቢኖርም እንዲያስተካክሉ እየጠየቅን አብረን እንሠራለን ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ኢትዮጵያ ከማንም በላይ ለጎረቤት ሀገራት የቅድሚያ ቅድሚያ ትሰጣለች ብለዋል፡፡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰውን የወደብ ስምምነት ተከትሎ በርካታ ጩኽት እና ሁካታ ይሰማል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለሶማሊያውያን ሁለተኛ ሀገራቸው ናት ብለዋል፡፡ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት እና ሀገረ መንግሥት ጽናት በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ውድ ሕይዎታቸውን ከፍለዋል ነው ያሉት፡፡
በሶማሊያውያን የጦርነት እና የመለያየት ዘመን ሁሉ መግለጫ ከማውጣት የዘለለ ፋይዳ ያልነበራቸው አንዳንድ ሀገራት አሁን ከሶማሊያ ጎን ለግጭት እንቆማለን ማለታቸው ለተልዕኮ ጦርነት ያላቸውን መሻት የሚያሳይ እንደኾነም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ማንንም ሀገር ወርራ አታቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ለመውረር መጥቶ ያሸነፈ አንድም ሀገር የለም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የሚያስችል በቂ አቅም እንዳላትም ተናግረዋል፡፡
ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞም ኢትዮጵያ አብሮ ለማደግ እና በጋራ ለመልማት ያላት ፍላጎት መቼም አይታጠፍም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው፡፡ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ግብጻውያን ወንድሞች ያላቸውን ማንኛውንም ጥያቄ በቅንነት ግልጽ ለማድረግ እና ለመነጋገር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መኾኗንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!