“እድገት እንዳለ ሁሉ የቆዩ የኢኮኖሚ ስብራቶችም አሉ፤ ለዚያ ነው ኢኮኖሚያችን በማደግ እና በመፈተን መካከል የወደቀው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

11

ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከሕዝብ እንደራሴዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ ጦርነት እና ዓለም አቀፍ ጫናዎች የማክሮ ኢኮኖሚያችንን በሚገባ ለመጠገን እንቅፋት ኾነው ስለመቆየታቸው ተናግረዋል።

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ በዕዳ መልክ ሲከማች የነበረው ሃብት አንደኛው የኢኮኖሚ ስብራት እንደነበር ገልጸዋል። ይህንን ለመቅረፍ ትርጉም ያለው ሥራ ስለመከናወኑ አመላክተዋል።

የገንዘብ ግሽበትን ለመቆጣጠር የገንዘብ ዝውውርን የመቀነስ እና ተቀማጭ ገንዘብን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። ይህም ግሽበትን በመጠኑ ስለመቀነሱ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብድር አገልግሎትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ170 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ስለመሰጠቱ ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ 83 በመቶው ለግሉ ዘርፍ ልማት የተሰጠ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ቀጣይነት ያለው እድገት እያመጣ ስለመኾኑም ተናግረዋል። በኢንዱስትሪው ዘርፍም “በኢትዮጵያ ታምርት” ንቃናቄ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

በአይሲቲ ዘርፍም ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል ብለዋል። በቅርብ ጊዜም ሁሉም ሃብት በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀስበት የካፒታል ገበያ ይጀመራል ብለዋል። የካፒታል ገበያ ሲጀመር ብዙ ሕጋወጥ የኾነ ሃብት ወደ ሕጋዊ መንገድ ገብቶ በርካታ ባለሀብቶችን ለመፍጠር ያስችላል ነው ያሉት። ይህንን ለማድረግም ተቋም ተቋቁሞ የሕግ ሥራዎች እየተጠናቀቁ መኾኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም 7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንደሚመዘገብ እንጠብቃለን ብለዋል። በምንፈልገው ልክ በመሥራት በኩል የሚቀር ነገር አለ፤ እሱን አስተካክለን መጓዝ ያስፈልጋል ነው ያሉት። “በዓለም ላይ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ጥቂት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተረጋገጠ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እድገት እንዳለ ሁሉ የቆዩ የኢኮኖሚ ስብራቶችም አሉ፤ ይህም ኢኮኖሚያችንን በማደግ እና በመፈተን መካከል ጥለውታል” ሲሉ ገልጸዋል።
የ2016 በጀት ዓመትን ገቢ እና ወጭዎችን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል። ባለፉት ስድስት ወራት የታቀደው የገቢ መጠን 270 ቢሊዮን ብር ነበር፤ ከዚህ ውስጥ 265 ቢሊየን ብር ገብቷል ብለዋል። ይህ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ17 በመቶ እድገት አለው። “በቂ ገቢ በሌለበት ሀገር ውስጥ በቂ ልማት መሥራት አይቻልም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገኘው የገቢ መጠን ካለን የኢኮኖሚ አቅም አንጻር ሲታይ አነስተኛ በመኾኑ ይህ መስተካከል እንደሚገባው አሳስበዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አምስት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ከተላኩ ሸቀጦች እና አገልግሎት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ስለመገኘቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሀገሪቱ ከውጭ ስላስገባችው የምርት እና አገልግሎት መጠን ሲገልጹም በአምስት ወር ውስጥ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የፈጀ ሸቀጥ እና አገልግሎት አስመጥተናል ብለዋል። ገቢ ንግድን በመተካት እና ወጭ ንግድን በማብዛት የውጭ ምንዛሬ አቅምን ማሳደግ አሁንም ያላለፍነው ስብራት ነው፤ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግማሽ ዓመቱ ከ1 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፤ ከ150 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ በውጭ ሀገራት ሕጋዊ የሥራ ሥምሪት ተጠቃሚ ኾነዋል ነው ያሉት። ሥራ ፈጠራ ላይ አሁንም ተጨማሪ ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡- አሜናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የልማት ሥራዎችን አጥፎም ቢኾን ሰው በድርቅ ምክንያት እንዳይሞት መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ማዕከሉ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)