“የልማት ሥራዎችን አጥፎም ቢኾን ሰው በድርቅ ምክንያት እንዳይሞት መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

33

ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ስለድርቅ ለተነሳው ጥያቄ እና የተሳሳተ አመለካካትን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ “ድርቁን እንደ ፖለቲካ ማየት ተገቢ አይደለም” ብለዋል፡፡

ድርቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 100 ዓመታት በተደጋጋሚ በየ10 ዓመቱ የሚከሰት እንደኾነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አሁን ላይ ደግሞ በየሦስት ዓመቱ የሚከሰት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

ይህ ሲባል ከአንድ ክልል አልያም ሀገር ተሻጋሪ ድርቅን እንጂ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ድርቅ በየዓመቱ እንደሚከሰት ተናግረዋል፡፡ ባለፉት 30 ዓመታትም ድርቅ ስለመኖሩ ገልጸው ጉዳዩ ግን ድርቅ መኖሩ ሳይኾን ሰው የመሞት ያለመሞቱ ጉዳይ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

ድርቅ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስም የችግኝ ተከላ እና ምርት በሰፊው በማምረት ችግሩን መቅረፍ እንደ መፍትሔ በመንግሥት በኩል ተወስደው ሲሠሩ እንደቆዩም አብራርተዋል፡፡
አሁን ላይ ድርቅ በአማራ፣ በትግራይ፣በኦሮሚያ እንዲሁም በምሥራቁ አንዳንድ አካባቢዎች ስለመከሰቱ ተናግረዋል፡፡ ድርቁን ግን እንደፖለቲካ ማየት ተገቢ እንደማይኾን ገልጸዋል፡።

ችግሩን መፍትሔ ለመስጠት ተባብሮ ሠርቶ ሰው እንዳይሞት ማድረግ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች ድርቅ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርብርብ በተሠራው ሥራ ሰው እንዳይሞት ስለመደረጉ ነው የተናገሩት፡፡

አሁንም ቢኾን በአማራ፣ በትግራይ ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ተረባርቦ ተጎጂዎችን ማገዝ እንደሚያስፈልግ ነው ያስረዱት፡፡
በመንግሥት በኩል የተወሰነም ቢኾን እርዳታ እየተደረገ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የተደረገውን ድጋፍ ችግር ላለባቸው አካባቢዎች በተቻለ መጠን የስርጭት ችግር እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡

ሰው ችግር ውስጥ እያለ መንግሥት ዝም እንደማይል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የልማት ሥራዎችን አጥፎም ቢኾን ሰው እንዳይሞት ድጋፍ እንደሚደረግ ነው ያረጋገጡት፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ በርሀብ የሚሞት ሰው የለም ብለዋል፡፡ አሁን ላይ በድርቅ ምክንያት የሚከሰት በሽታ ስለመኖሩ እና ይህም ለሞት ሊያደርስ እንደሚችል እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ በታሪካ ከመቸውም ጊዜ በላይ ተመርቶ የማያውቅ ምርት ስለመኖሩ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመስኖ ከሚለማው ማሳ ከ120 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል፡፡

ይህን ያመረተ አርሶ አደር ወንድሙ ተርቦ ዝም ብሎ እንደማያይ ነው የተናግሩት፡፡ ይህ ስንዴ መመረቱ የሚያማቸው እንዳሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ለማራከስ የሚደረገው ጥረት ግን ተቀባይነት እንደሌለው አስገንዝበዋል፡፡

በማረስ እና በማልማት ግን ራስንም ሀገርንም መጥቀም እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡ አሁን ላይ ግን ከ1977 ዓ.ም በላይ ድርቅ አለ በማለት ሀገርን ለማራከስ የሚደረገው ጥረት ተገቢ እንዳልኾነ ተናግረዋል፡፡

በምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሐሰት እና የጥላቻ መረጃዎች መሰራጨት የኢትዮጵያን ፈተና አብዝቶታል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“እድገት እንዳለ ሁሉ የቆዩ የኢኮኖሚ ስብራቶችም አሉ፤ ለዚያ ነው ኢኮኖሚያችን በማደግ እና በመፈተን መካከል የወደቀው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)