
ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
“የኢትዮጵያ ፈተና ለምን በዛ?” በሚል ከሕዝብ እንደራሴዎች ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄው ተገቢ እና ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፈተና መብዛት ምክንያቶች ባሏቸው ነጥቦች ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተለይም በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሀገረ መንግሥት ታሪክ ውስጥ መንግሥታት እንቅፋት ይኾኑብኛል ብለው ያሰቧቸውን ግለሰቦች የሚይዙበትን አግባብ እና እኛ ጉዳዩን የምናይበት እና የምናስተናግድበት መንግድ ልዩነት አለው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው፡፡
“መግደል ቀርቶ ማሳር እንኳን” ብዙ ርቀት ሄደን ነው የምንፈጽመው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀላሉን መንገድ ከመምረጥ ይልቅ ከባዱን፤ ነገር ግን ዘላቂውን እና አዋጩን መንገድ እየተከተልን ነው ብለዋል፡፡ በተቻለ መጠን ከእነክፍተቶቹም ቢኾን መንግሥት ዴሞክራሲያዊ መኾኑ ፈተናውን እንዲበዛ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ሌላው የኢትዮጵያ ፈተና የበዛው የብዙኅን መገናኛ ተቋማት በግለሰቦች እጅ እስኪገቡ ድረስ መበራከታቸው ነው ብለዋል፡፡ መረጃ በብርሃን ፍጥነት ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ በሚሰራጭበት በዚህ ዘመን የሐሰት እና የጥላቻ መረጃዎች መሰራጨት የኢትዮጵያን ፈተና አብዝቶታል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ሌላው የኢትዮጵያ ፈተና መብዛት ምክንያቱ ገንዘብ እንደኾነ አንስተዋል፡፡ የገንዘብ ስርጭቱ ከፍ እያለ መጥቷል፤ ብር ውስን ነው ማለት ደግሞ ጥይት ውስን ነው ማለት ነው ብለዋል፡፡ ገንዘብ ከጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች እና ከሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞም ይቀርባል ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያን ጠንካራ ሀገር ኾኖ መውጣት የማይፈልጉ ኃይሎች በዙሪያችን ይኖራሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገንዘብ አውጥተው ሚዲያ ያቋቁማሉ ብለዋል፡፡ ገንዘብ ለሚያወጡት ሀገራት ሀገር ማፍረስ፤ ሚዲያ ለሚቋቋምላቸው ደግሞ ቢዝነስ ኾኗል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው መንግሥት ችግር ይኖርበታል ሊወቀስም ይችላል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን የሚወቅሱት መንግሥት አላቸው፤ የሚወቅሱት መንግሥት የሌላቸው ሀገራት ስላሉ ነገሮችን ሰፋ አድርጎ መመልከት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!