13

አዲስ አበባ: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 9 እና 10/2016 ዓ.ም እንዲሁም 44ኛው የአባል ሀገራቱ የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ሥብሠባ ደግሞ ከመሪዎች ጉባኤ ቀደም ብሎ የካቲት 6 እና 7/2016 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤውን የምታዘጋጀው መሥራች እና አባል ሀገሯ ኢትዮጵያም በመዲናዋ አዲስ አበባ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች መኾኑን የአዘጋጅ ብሔራዊ ኮሚቴው ገልጿል።የእስካሁን የተግባር ሥራዎቹን ሪፖርት ለመገናኛ ብዙኃን የሰጠው ብሔራዊ ኮሚቴው አዲስ አበባ ለእንግዶቿ ሁሉን አቀፍ ምቾት እና እረፍትን የምትሰጥ እንድትኾን ብሔራዊ ኮሚቴው በከተማ ገጽታ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች በትራንስፖርት፣ በሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም መሰል ተግባራት ላይ በስፋት እየተሠራ ይገኛል ተብሏል።

በእስካሁን የተግባር ሂደቱ የከተማ ማስዋብ፣ የተቋማት ዝግጅት እና መሰል ተግባራት ላይ በስፋት መሠራቱን የገለጹት የብሔራዊ ኮሚቴው ሠብሣቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ 35 የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ተቋማትን ያቀፈው ብሔራዊ ኮሚቴ ተግባሩን በማጠናቀቅ ሂደት ላይ ነው ብለዋል።

በዘንድሮው የኅብረቱ ጉባኤም 21 በፕሬዚዳንቶች፣ 3 በምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ እንዲሁም 1 በንጉሥ እና 1 በውጪ ጉዳይ የሚመራ የሀገራት ልዑክ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የዘንድሮው የኅብረቱ ጉባኤ በትምህርት ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚመክር ያነሱት በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕከተኛ አምባሳደር አየለ ድሪር ናቸው፡፡ ቋሚ መልዕከተኛው “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ሥርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራት እና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት” የሚል መሪ መልእክት አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከኅብረቱ ጉባኤ ባሻገር ሁለት የጎንዮሽ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀቷን አምባሳደር አየለ አንስተዋል።ዲጂታል ኢኮኖሚን በመጠቀም ለውጥ ማምጣት እና አፍሪካ ራሷን በምግብ ትችላለች በሚል በመሪዎች ደረጃ ውይይቶችን ለማድረግ እድሎች ተመቻችተዋል ተብሏል።

ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራን ሕዝብ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ 53 የመንገድ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ ገብተዋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“የሐሰት እና የጥላቻ መረጃዎች መሰራጨት የኢትዮጵያን ፈተና አብዝቶታል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)