“የአማራን ሕዝብ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ 53 የመንገድ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ ገብተዋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

29

ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአማራ ሕዝብ ከሚነሱ ሦስት አንኳር ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የልማት ጥያቄ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልማትን ከማረጋገጥ አኳያ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መመለስ አለብን፤ ጥያቄዎቹን ቸል ብሎ በማለፍ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም በሚል ጥያቄዎቹ ተደራጅተው ባለፉት አምስት ዓመታት በአማራ ክልል 53 የመንገድ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች 3 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ውስጥ 1ሺህ 300 ኪሎ ሜትር መጠናቀቁን አስገንዝበዋል፡፡

ጎንደር እና ጎጃምን የሚያገናኘው ድልድይ ከእድሜ መግፋት የተነሳ አንድ ቀን ሊፈርስ ይችላል በሚል ሌላ ድልድይ እንዲሠራ ጥያቄ ሲቀርብ መቆቱን አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ የተገነባው እጅግ ዘመናዊ የኾነ ድልድይ በመኾኑ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄ ያለውን ክብር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

አሁን የተገነባው ይህ ድልድይ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጭ ተደርጎበታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም በሀገሪቱ ይህን ያህል ወጭ ተደርጎ የተሠራ የመጀመሪያው ድልድይ እንደሚያደርገውም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ድልድዩ በአማካኝ 50 ሜትር ስፋት እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

በሁለት መንገድ ሦስት ሦስት መኪና የሚያሳልፍ እንደኾነም ነው ያብራሩት፡፡ በሁለት መንገድ ስፋታቸው ሦስት ሜትር የኾኑ የብስክሌት ማሳለፊያ እንዳለውም አስገንዝበዋል፡፡ ለእግረኛ የሚኾን 5 ሜትር መንገድ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ይህ የኾነበትም ምክንያት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ይገባል ከሚል እሳቤ እንደኾነ መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሁሉ አንድም የሽሮ ፈሰስ የሚባሉ መንገዶች እንደሌሉ ለጊዜው ሳይኾን ለትውልድ እንዲሻገር ተደርጎ እየተሠሩ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ በመንገድ ፕሮጀክቶቹ መንግሥት የሚሠራቸውን የመንገድ ጥገና ሥራዎችን እንደማይጨምርም አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ከቀረበው የልማት ጥያቄ አኳያ በቂ ነው ባይባልም ልማትን ለማረጋገጥ ግን ማሳያ እንደኾነ ነው ያብራሩት፡፡ አማራ ክልል ትልቅ ክልል በመኾኑ ብዙ የልማት ሥራዎች ሊሠሩበት የሚገባ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡

በምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕገ መንግሥቱ እኛ ስንለቅ አብሮ የሚቀደድ ሕገ መንግሥት እንዳይኾን ቅድሚያ ብንመክር ይሻላል በሚል እየሠራን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article