“ሕገ መንግሥቱ እኛ ስንለቅ አብሮ የሚቀደድ ሕገ መንግሥት እንዳይኾን ቅድሚያ ብንመክር ይሻላል በሚል እየሠራን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

25

ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛውን መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እየተካሄደ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላቱ ምላሽ እና ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሕዝብ እንደራሴዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ወቅታዊ የፀጥታ ችግር አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ሦስት ናቸው ብለዋል፡፡

አማራ ክልል ሁሉንም ዞኖች ሊባል በሚችል መልኩ የማነጋገር እድል ነበረኝ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ልማት፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እና የወሰን ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡ የሕዝቡን የመልማት ፍላጎት እና ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡

ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ሌሎች ክልሎችም ጥያቄ አላቸው ነው ያሉት፡፡ ደርግ የንጉሠ ነገሥቱን ሕገ መንግሥት ቀድዶ የራሱን፤ ኢሕአዴግ የደርግን ቀድዶ የራሱን ሕገ መንግሥት እንዳረቀቁ ሁሉ አሁን ያለው መንግሥት ተመሳሳይ ችግር ላለመሥራት እየሠራ ይገኛል፤ የተሻለ መፍትሔ ለማምጣትም እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

“ሕገ መንግሥት ከመንግሥታት ጋር የሚቀየር እና የሚቀደድ መኾን የለበትም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ ስንለቅ አብሮ የሚቀደድ ሕገ መንግሥት እንዳይኾን ቅድሚያ ብንመክር ይሻላል በሚል ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በቅንነት ማገዝ ይገባል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው የአማራ ሕዝብ ሦስተኛው ጥያቄ የወሰን ጉዳይ መኾኑን አንስተው ችግሩ ዘላቂ ሰላምን በሚያረጋግጥ መልኩ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሰላም ችግሮቻችን የኢትዮጵያን አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ያደረጉ አይደሉም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“የአማራን ሕዝብ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ 53 የመንገድ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ ገብተዋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)