“የሰላም ችግሮቻችን የኢትዮጵያን አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ያደረጉ አይደሉም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

39

ባሕርዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛውን መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እየተካሄደ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላቱ ምላሽ እና ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሕዝብ እንደራሴዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡ አሁናዊውን ሀገራዊ እና ቀጣናዊ የሰላም ሁኔታ መንግሥትዎ እንዴት ያየዋል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአንድ ሀገር እድገት እና ብልጽግና ሰላም ቁልፉ እና ዋናው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ የሰላም እጦት በርካታ ችግሮችን እየፈጠረ እንደኾነም አንስተዋል፡፡

“የሰላም ችግሮቻችን የኢትዮጵያን አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ያደረጉ አይደሉም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም እጦት ችግሮች ያሏቸውን ዐበይት ምክንያቶች ጠቁመዋል፡፡

የመጀመሪያው የፖለቲካ ፍላጎት ማሳኪያ ልምምዳችን ችግር እና ስብራት ያለበት መኾኑ ነው ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ልዩነትን በሃሳብ ልዕልና ከማሸነፍ ይልቅ አፈሙዝ መምዘዝ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የመጣንበት መንገድ መኾኑን አንስተዋል፡፡

ሁለተኛው ልዩነቶቻችን በመወያየት፣ በመነጋገር እና በሽምግልና ችግሮች የመፍታት ባሕላችን እየቀነሰ መምጣቱ አንድ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ ችግሮችን በሰከነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ግጭትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መውሰድ ለሰላም እጦቱ እንደ ምክንያት ተነስቷል፡፡

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጠረው የሰላም እጦት ሦስተኛው ምክንያት በሰላም መንገዶቻችን ላይ ወጥመድ እና መሰናክል እያስቀመጡ መሄድ ችግር ኾኗል ብለዋል፡፡ ችግሮችን ለመፍታት እና ልዩነትን ለማጥበብ ከግጭት ይልቅ ሰላማዊ የመነጋገር እና በሃሳብ የበላይነት የማሸነፍ ልምምድን ማምጣት ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በአባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛል።
Next article“ሕገ መንግሥቱ እኛ ስንለቅ አብሮ የሚቀደድ ሕገ መንግሥት እንዳይኾን ቅድሚያ ብንመክር ይሻላል በሚል እየሠራን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)