
ባሕር ዳር: ጥር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር ለመዝናናት የምትመች ብዙ አግራሞትን የሚያጭሩ ክስቶች የሚስተዋልባት ከተማ ናት። እኔ ከተማዋን እየዞርኩ የመቃኘት ልምድ አለኝ ዛሬም እደወትሮየ በከተማዋ ስዘዋወር ከምመለከታቸው ብዙ ለትዝብት ከሚኾኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱን መርጨ ሃሳቤን ላካፍል ወደድኩ፡፡
ውቢቱ ባሕር ዳር እውነትም ለነዋሪዎቿም ይሁን በድንገት በእንግድነት ለተገኘ ውብ ከተማ ለኑሮ የተመቸች እንደኾነች በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል፡፡ የሕዝቦቿ እንግዳ ተቀባይነት እና ገራገርነት ደግሞ ከተማዋ ይበልጥ እንድትመች አድርጓታል፡፡
እኔም በከተማዋ ስዘዋወር አግራሞትን የሚያጭሩ ብዙ ጉዳዮችን ባስተውልም አንድ ነገር ግን በትዝብት እንድቃኘው ግድ ብሎኛል፡፡ሥርዓት በሚያውቅ ሕዝብ ውስጥ ድንገት ከዛ የዘለለ ክስተት ሲታይ እንግዳ ይኾናል እና አግራሞትን ማጫሩ አይቀርም፡፡
ከተማዋን እየዞርኩ ስመለከት በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚተረማመሱ እና መንዱን ግጥም አድርገው ዘግተው “ጋሽየ በቅናሽ ውስድ” የሚሉ ልብስ፣ ጫማ እና መሰል እቃዎችን ይዘው የሚሯሯጡ ወጣቶችን ማስተዋሌ ጉዳዩን በጥልቀት እንድመረምር አድርጎኛል፡፡
በከተማዋ የሚካሄደው ሕገ ወጥ ንግድ በከተማዋ ያሉትን የሚያማምሩ መንገዶች ውበት እንዳይታይ ከማድረጉም ባለፈ የሚንቀሳቀሰውን ሰው እንዳሻው እንዳይዘዋወር አድርጎታል፡፡ የሚካሄደው ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በሕጋዊ ለሚንቀሳቀሱ የንግድ ሱቆችም የራስ ምታት መኾናቸውን ታዝቤአለው፡፡
አብዛኞቹ ግብር እየከፈሉ በሕጋዊ መንገድ ሱቅ ተከራይተው የሚሠሩ ሰዎች ድርጊቱ እየጎዳቸው እንደኾነ በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡ሕጋዊ ነጋዴዎች ደንበኞቻቸውን በሕገ ወጥ ነጋዴዎች ተቀምተው ምንም ሳይገበዩ ውለው እንደሚሄዱም ማስተዋል ይቻላል፡፡ ይህን አስተውሎቴን ለማረጋገጥ ወደ አንደኛው ሱቅ ቀረብ ብየ ስለጉዳዩ ጠየኩት የሚየደርጉት ቸግሯቸው እንጅ ደንበኞቻቸውን እየነጠቁ ሳይገበዩ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ነገሩኝ፡፡
ይህ ክስተት ደግሞ ነገ በሚከፍሉት ግብርም ኾነ በእለታዊ የቤተሰብ ኑሯቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝም ነው የሚገልጹት፡፡ እያንዳንዱ ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ነጋዴ ከሱቆቹ በተወሰነ ብሮች ቅናሽ ያለው በመኾኑ ሰዎች ከእነዚህ ሕገ ወጦች እንዲገበያይ አድርጎታል፡፡
አብዛኛው ማኅበረሰብ በቀጥታ አያግኘው እንጅ ከግብር በሚሰበሰበው ገንዘብ በሚሠራው መሠረተ ልማት ማለትም ከትምህርት ቤት፣ ከጤና ግንባታ፣ ከግብርና ማሻሻል፣ ከሥራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንደሚኾን የሚያስበው ሰው በጣም ውስን ነው፡፡
ግብር የሚከፍሉ እና በሕጋዊ መንገድ የሚነግዱ ሰዎች ከገበያው በወጡ ቁጥር የሚጎዳው ራሱ ማኅበረሰቡ እንደኾነ ተገንዝቦ ከሕገ ወጦቹ አልገዛም ብሎ የሚያስብም አይታይም፡፡ አብዛኛው ሰው ለእለቱ ከእቃዎቹ የሚያገኘውን ሽርፍራፊ ሳንቲም ከማሰብ በዘለለ አርቆ ማየትን አልቻለም፡፡
እነዚህ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች እቃዎቹን ከየት እንደሚያመጡት ለመጠየቅ ሞክሬ ነበር፡፡ ሕገ ወጥ ሥራውን ከሚከለክሉ ሕግ አስከባሪዎች ለማምለጥ ከሚጣጣሩ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች መካከል አንደኛው በችኮላ እና ግራ ቀኙን ሕግ አስከባሪዎች እንዳይዙት እየቃኘ ከትልልቅ ባለሃብቶች እቃዎቹን በኮሚሽን እየታሰበላቸው እንደሚያገኙ ነገረኝ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ትልልቅ ነጋዴዎች እቃዎችን እያቀረቡ ሥራውን ማሠራታቸው ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
ትልልቅ ነጋዴዎች ግብርን ለመሰወር እንዲያመቻቸው ይህን አሠራር እንደሚከተሉም ሰማሁ፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት ሕገ ወጥ ነጋዴ ተቆጣታሪዎችን እንዳሰማራ ሕገ ወጥ ነጋዴዎቹ ሰምቻለሁ፤ ሕገ ወጥ ነጋዴዎቹም ያውቃሉ፡፡ በተለይ እነዚህ ሕግ አስከባሪዎች ከሕገወጦች ጋር አንዱ ለመያዝ ሌላው ደግሞ ተይዞ ላለመታሰር የሚያደርጉትን እሩጫ እና መተረማመስ ለተመለከተ ደግሞ ሌላ አሳዛኝ ትዕይንት ይኾናል፡፡
ከተማ አሥተዳደሩ ሕገ ወጦችን በሕገ ወጥ ተቆጣጣሪዎች ብቻ ማስቆም እንደማይቻል ግን የገባው ይመስላል፡፡ ለዚህም ሕገ ወጦች በሕጋዊ መንገድ እንዲነግዱ ለማስቻል የእሁድ ገበያን ተግባራዊ አድርጓል፡፡
የእሁድ ገበያ አሠራር ሕገ ወጦችን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይችልም በተወሰነ መንገድ ግን መቀነስ እንደተቻለ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጅ ይህም አሠራር ቤተሰብ ላላቸው እና ቤት ተከራይተው ለሚኖሩ ሰዎች የአንድ ቀን ንግድ በቂ ባላመኾኑ ቅዳሜ ገበያንም ማማተራቸው አልቀረም፡፡
በዚህ የአማራጭ ንግድ ውስጥ ብዙዎች ተጠቃሚ እና ከስጋት ነጻ መኾን እንደቻሉም አይቻለሁ፡፡ በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩ ሰዎችም አሁን ላይ የተሻለ ገበያ ማግኘት የቻሉ በመኾኑ አሠራሩን አጠናክሮ መቀጠል ለከተማዋ ሕዝብም ኾነ ለነጋዴው ማኅበረሰብ የሚሰጠው ጥቅም ከፍ ያለ በመኾኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ይሰማኛል፡፡
ማኅበረሰቡም በሕጋዊ መንግድ የሚነግዱት ነጋዴዎችን ከሕገ ወጦቹ በተሻለ የረጅም ጊዜ ጥቅም እና ለሀገር እድገት ያላቸውን ፋይዳ በማስተዋል በሕጋዊ መንገገድ ከሚነግዱትም ኾነ ከተማ አሥተዳደሩ ካቋቋመው የእሑድ ገበያ ገብይትን በመፈጸም ማበረታታት ይጠበቅበታል፡፡
ካፒታል ጋዜጣ በአንድ ወቅት የጎዳና ሕገ ወጥ ንግድ የሀገሪቱን 38 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ገቢ እንደሚሽፍን አስነብቦ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡ በዚህ መንገድ እስከ መቼ? በአማላይ ቃላት የሚፈጸም ሕገ ወጥ ተግባር መቼ ይዘጋ ይሆን?
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!