
ደሴ: ጥር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእናቶችን ጤና ለማስጠበቅ በጋራ ትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገልጿል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ 14ኛውን ክልል አቀፍ የጤናማ እናትነት ወር በኮምቦልቻ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እክብሯል።
“ፍትሐዊ ተደራሽ እና ጥራት ያለው የቅድመ ወሊድ ክትትል በወቅቱ በማስጀመር ጤናማ እንትነትን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው። በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ውብሸት ብርሃኑ እና የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሲስተር አስካል ደምሴ
በአካባቢው ያለው አንጻራዊ ሰላም የእናቶችን ጤና በመጠበቁ ረገድ ቀልጣፋ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ እንዳስቻላቸው ጠቅሰዋል። ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ጠንካራ ሥራ ለመሥራትም ማቀዳቸውን አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ አበበ ተምትሜ በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሁሉም አካባቢዎች የጤና አገልግሎት ተደራሽ ባለመኾኑ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት ሕመም፣ የተራዘመ ወይም የተስተጓጓለ ምጥ፣ ኢንፌክሽ እና ጥንቃቄ የጎደለው የጽንስ መቋረጥ ለእናቶች ሞት ዋና መንስኤ መኾናቸውን ገልጸዋል። እነዚህ የሞት መንስኤዎችን አስቀድሞ በመከላከል የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከአጋር አካላት እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር እየተሠራ መኾኑንም አመላክቸዋል።
ምክትል ቢሮ ኀላፊው የተቀላጠፈ እና በሁሉም ቦታ ተደራሽ የሚኾን የእናቶች ጤና አገልግሎት እንዲኖር ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ “በሀገር ውስጥ የፋይናንስ አቅም የቤተሰብ ዕቅድ አማራጮችን ማስፋት” በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም የቤተሰብ እቅድ ቀንን ለመጀመሪያ ጊዜ እያከበረም ይገኛል።
ዘጋቢ:- ሕይወት አስማማው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!