የፍጹም ቅጣት ምቱ “ዘበኛ!”

72

ባሕር ዳር: ጥር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሮን ሄይደን ዊሊያምስ ይባላል፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ጥር 21/1992 ደቡብ አፍሪካ ፖርት ኤልዛቤት ከተማ ነው የተወለደው፡፡ 1 ሜትር 84 ሴንቲ ሜትር ቁመት አለው መለሎ ነው፡፡

ይህ ብላቴና በመኖሪያ ሰፈሩ የእግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች ሲሰለጥኑ ይመለከታል፡፡ ከግብ ጠባቂው ጀርባ ኾኖም ኳስ በተከታታይ ያቀብላል፡፡ በዚህም ደስተኛ ነበርኩ ይላል።
ከእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል ለግብ ጠባቂዎች የተለየ ምልከታ ነበረው፡፡ በመኾኑም ከትምህርቱ ጎን ለጎን እግር ኳስ በመጫወት ጊዜውን ያሳልፋል፡፡

ውሎ ሲያድር ብላቴናው የእግር ኳስ ተጫዋች ለመኾን ተስፋ ሰነቀ፡፡ ፍላጎቱን እና ዝንባሌውን ያስተዋሉት ቤተሰቦቹ ደግሞ ሱፐር ስፖርት አካዳሚን ተቀላቅሎ እግር ኳስን እንዲሰለጥን አደረጉት፡፡

ከስልጠናው ማግስትም በተለያዩ የወጣት ቡድኖች ተመልምሎ ተጫውቷል፡፡ ሻተርፕሩፌ ሮቨርስ፣ ለቶተንሃም ሆትስፐር እና ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ወጣቱ ሮን ሄይደን ዊሊያምስ የተሰለፈባቸው ቡድኖች ናቸው፡፡

የሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ቡድን ደግሞ ብቃቱን ገምግሞ ከ2010 ጀምሮ በዋናው ቡድን እንዲሰለፍ አደረገው፤ በቡድኑም እስከ 2022 ለ12 ዓመታት በ278 ጨዋታዎች ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡

በ2022 የተሻለ ክፍያ ያቀረበለትን የማሜሎዲ ሰንዳውንስ ቡድን ተቀላቀለለ፡፡ በ32 ጨዋታዎችም ተሰልፏል፤ አሁንም እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ዊሊያምስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው እ.ኤ.አ በ2014 ከብራዚል ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ነበር፡፡ እስካሁንም በ40 ጨዋታዎች ተሰልፎ ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ነው፡፡

በ2021 የባፋና ባፋና አሰልጣኝ ሁጎ ብሩስ ዊልያምስን አምበል አድርገው ሾሙት፡፡ በ34ኛው አፍሪካ ዋንጫ ዊልያምስ የደቡብ አፍሪካ አምበል ነው፡፡
ባፋና ባፋና ከብሉ ሻርኮች ጋር ባደረገችው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ በተጨማሪው 30 ደቂቃም ዜሮ ለዜሮ በመለያየታቸው ጨዋታውን በፍፁም ቅጣት ምት መቋጨት ግድ ብሏል፡፡
እናም ኬፕቨርዴዎች የመቱትን አራት የፍፁም ቅጣት ምት ዊሊያምስ በማዳን አድናቆት ተችሮታል፡፡

ደቡብ አፍሪካም እንደ አውሮፖዊያን አቆጣጠር ከ2000 በኋላ የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግማሽ ፍፃሜው እንዲያልፍ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡
አሰልጣኝ ሁጎ ብሩስ “ዊሊያምስ ብሔራዊ አርበኛችን ነው፤ በግማሽ ፍጻሜው ብንሸነፍ እንኳ የእሱን የጀግንነት ከፍታ አናወርደውም፡፡ ለዊሊያምስ የክብር ሐውልት ሊገነባለት ይገባል፤ መንገድ ወይም የትምህርት ተቋማት በስሙ ሊሰየምለት ግድ ነው”በማለት አሞካሽተውታል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማውሪሲዮ ፖቸቲኖ ከቼልሲ የመሰናበት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
Next articleየእናቶችን ጤና ለማስጠበቅ በጋራ ሊሠራ እንደሚገባ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።