መገናኛ ብዙኀን ለሀገር ጥቅም የሚበጁ እና ኀላፊነት የተሞላባቸው መረጃዎችን ለሕዝብ በማድረስ ሀገርን መገንባት እንደሚገባ የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ገለጸ፡፡

13

ደሴ: ጥር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መገናኛ ብዙኃን ወቅታዊ ሁኔታውን በመረዳት ለሀገር ጥቅም የሚበጁ እና ኅላፊነት የተሞላባቸውን መረጃዎች ለሕዝብ በማድረስ ሀገር መገንባት እንደሚገባ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገልጿል። ቢሮው የስድስት ወር መደበኛ እና ወቅታዊ ሥራቹን የእቅድ አፈጻጸሙን በኮምቦልቻ ከተማ እየገመገመ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሕሌና መብራቱ የመድረኩ ዓላማ ባለፉት ስድስት ወራት የተሳኩ ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠል እና ድክመት የታየባቸውን ለማስተካከል እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር መገናኛ ብዙኀን ኀላፊነት ተሰምቷቸው የሚሠሩበት ጊዜው አሁን እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡በመድረኩ የክልሉን የስድስት ወር እቅድ ያቀረቡት የቢሮው የእቅድ ዝግጅት ክትትል እና ግምገማ ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ፍሬሕይወት ተፈራ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አሁናዊ ሁኔታን የተመለከት ሰነድ አቅርበዋል።

ዳይሬክተሯ ተቋማቸው የቀውስ ጊዜ የዘገባ ስልትን በመጠቀም ለኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃን መስጠት እንደሚጠበቅበት ነው የተናገሩት። ማኀበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በክልሉ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማባባስ በርካታ ሀሰተኛ መረጃዎች እንደሚሰራጩ ጠቁመው የዲጂታል ሚዲያውን ተጽዕኖ በመቋቋም ረገድ ሕዝብ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል። የተሳሳቱ እና አፍራሽ መረጃዎችን በመመከት ትክክለኛውን ገጽታ መገንባት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- አበሻ አንለይ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከወቅታዊ ሁኔታው አንፃር የብዙኃን መገናኛ ኀላፊነት ተሰምቷቸው የሚሠሩበት ጊዜው አሁን እንደኾነ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገለጸ፡፡
Next articleምክር ቤቱ 14ኛ መደበኛ ጉባዔውን ነገ ከጠዋቱ 2፡00 ጀምሮ ያካሂዳል፡፡