
እንጅባራ: ጥር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሴቶች ክልሉ ከገባበት የሰላም እጦት እንዲወጣ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አሳስቧል።”የኢትዮጵያን ሰላም አስጠብቃለሁ ለልጆቼ ምንዳን አወርሳለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ዘላቂ ሰላምን በማጽናት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ የንቅናቄ መድረክ በእንጅባራ ከተማ ተካሂዷል።
የንቅናቄ መድረኩን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት በጥምረት አዘጋጅተውታል። በመድረኩ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ያላረጋገጠ ሰላም እና ልማት እውን ሊኾን እንደማይችል ገልጸዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሴቶችን ተሳትፎ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።ሴቶች ከፈጣሪ የተሰጣቸውን የእናትነት ፀጋ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ከበሬታ በመጠቀም ክልሉ ከገባበት የሰላም እጦት እንዲወጣ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም ዋና አሥተዳዳሪው አሳስበዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተናኘወርቅ መኮነን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ብሎም በክልሉ ያጋጠመው የሰላም እጦት በሴቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል። ሴቶች ለሀገር ሰላምና ልማት ያላቸውን አበርክቶ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባልም ብለዋል ኀላፊዋ።
የመድረኩ ተሳታፊ ሴቶችም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።በመድረኩ ማጠቃለያ ላይም የሀገር ምልክት ለኾነው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የዞንድ ግዥ ተከናውኗል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!