
ባሕር ዳር፡ ጥር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ እና የዞን ከፍተኛ አመራሮች በፋብሪካው ተገኝተው የሚገኝበትን የግንባታ ሁኔታ ተመልክተዋል። የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ አበባው በቀለ ፋብሪካው በቅርብ ጊዜ ወደ ምርት ይገባል ብለዋል።
ፍብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በቀን ከ130 ሺህ እስከ 150 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ያመርታል ነው ያሉት። እስከ 20 ሺህ ለሚኾኑ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተሞች ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ.ር) በአፍሪካ ግዙፉ የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክተናል ብለዋል።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ለግንባታው ዘርፍ እንቅፋት የኾነውን የሲሚንቶ እጥረት የሚፈታ ትልቅ ፕሮጀክት እንደኾነም አስረድተዋል። ከመንገድ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ለዓለም ለይኩን።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!