
ደብረ ብርሃን: ጥር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ታጣቂዎች ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል።
ታጣቂዎቹ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን ተከትሎ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተሞች ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሰላም የመጡትን አመሥግነዋል።
ዶክተር አህመዲን እንሳሮ ወረዳ ትልቅ የልማት አቅም ያለው አካባቢ በመኾኑ ይህንን ሃብት መጠቀም የሚቻለው በሰላም ብቻ መኾኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ የሕዝቡ ጥያቄ ላይ ልዩነት ባይኖርም የአፈታት መንገዱ ላይ በተፈጠረ ልዩነት ብዙ ዋጋ ተከፍሏል ብለዋል።
የግጭት አካሄድ ችግሮችን ለመፍታት አያስችልም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በቀጣይም የሰላም አማራጭን በመከተል ወደ ሰላም መመለስ እንደሚያስፈልግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የተመለሱ ወጣቶችም መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄ አሁንም መመለስ ይኖርበታል ብለዋል። መንግሥት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ተነሳሽነቱን ካሳየን ለማገዝም ዝግጁ ነን ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ለዓለም ለይኩን።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!