
ፍኖተሰላም: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።
“ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ መልእክት ሕዝባዊ ውይይት በፍኖተ ሰላም ከተማ ተካሂዷል።
ሕዝባዊ ውይይቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፣ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ቢቄላ ሁሬሳ (ዶ.ር) እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጌታሁን አብዴሳ መርተውታል።
ከፍኖተ ሰላም ከተማ እና ከምዕራብ ጎጃሞ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡት የሕዝባዊ ውይይቱ ተሳታፊዎች ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥያቄዎችን ለአወያዮቹ አቅርበዋል። የሰላም እጦት፣ መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች አለመመለስ፣ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ እድል ፈጠራ አለመኖር፣ ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት፣ የዜጎች መፈናቀል እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለአወያዮቹ የቀረቡ ጥያቄወች ማዕከል ናቸው።
ከተወያዮቹ ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ የሰጡት አወያዮችም የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የመላው ኢትዮጵያዊያን ጥያቄዎች ናቸው ብለዋል።
የአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ሕዝቦች ለዘመናት የጸና እና የተጋመደ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው ያሉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጌታሁን አብዴሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠሩ ችግሮችን ከምንጫቸው ለማድረቅ እየተሠራ ነው ብለዋል። ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚሰራው ሥራ ውጤታማ መኾኑንም አንስተዋል።
“የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ነው፤ የአማራ ሕዝብ ሰላም ማጣት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ማጣት ነው” ያሉት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ቢቄላ ሁሬሳ (ዶ.ር) ናቸው። በአማራ እና ኦሮሞ ሕዝቦች መካከል ያለው መስተጋብርም ከማንነት የላቀ ትስስር አለው ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ግልጽ፣ ታውቀው ያደሩ እና በፌደራል መንግሥት የተያዙ ናቸው ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ሕጋዊ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የሕዝብን ጥያቄ ሽፋን አድርጎ ሕዝብን ማወክ ተገቢ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር ለሕዝብ ሰላም ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት። አወያዮቹ በውይይቱ የተነሱ ጥያቄዎችን በመያዝ ለተግባራዊ ምላሹ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!