“የፌዴራል መንግሥት ከማንም ጋር በሰላም ችግሮችን የመፍታት ፍላጎት አለው” አቶ አሕመድ ሽዴ

24

ደብረታቦር: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ኀብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ መልእክት ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱን የመሩት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ከሕዝብ ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ርስቱ ይርዳው የአማራ ሕዝብ እጅግ የምንኮራበት እና የኢትዮጵያ መሠረት ነው ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ስለ ሀገር ክተት ሲባል ቀድሞ በመገኘት ሀገርን ያጸና ሕዝብ መኾኑንም አንስተዋል።

የእርስ በእርስ መጠፋፋት አይጠቅም፣ ወደ ሰላም መመለስ ይገባል ብለዋል። ስለ ሰላም አብረን እንቁም ያሉት አቶ ርስቱ እኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብ ሀገርና ሕዝብ እንደማይጠቅም ተናግረዋል። ሕዝብን የሚያሰቃይ የትኛውም አካል የሕዝብ ጠላት መሆኑንም ተናግረዋል። እጃችን ስለ ሰላም የተዘረጋ ነውም ብለዋል። የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን ምክር የማይሰማ እና የሚያዋርድ አካል ለሕዝብ እንደማይጠቅምም ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ ችግር ይገደናል፣ ልንደርስለት እና ችግሩን ልንፈታው ግዴታ አለብም ብለዋል።

ስለ ሰላም በአንድነት መሥራት እና ሰላም የተጠማውን ሕዝብ ሰላም ማድረግ ግዴታ እንደኾነም አሳስበዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንሠራለን ብለዋል። በክልሉ ለተፈጠረው ችግር እንደዋና አጀንዳ ተደርጎ የሚወሰደው የክልል ልዩ ኃይሎች እንደገና መዋቀር በአማራ ክልል ብቻ የተደረገ አለመኾኑን አስታውቀዋል። ያለን ሀገር ኢትዮጵያ ናት ያሉት አቶ አሕመድ ኢትዮጵያ ደግሞ አንድ ጠንካራ የጸጥታ ኀይል ያስፈልጋታል ነው ያሉት። በአማራ ክልል ላይ የተፈጠረው የአፈጻጸም ችግር የፈጠረው ካልኾነ በስተቀር የአማራ ክልልን ብቻ የሚጎዳ አካሄድ ፈጽሞ የለም፣ አይኖርምም ብለዋል።

የፌዴራል መንግሥት በአማራ ክልል ብቻ የተለየ አካሄድ ያደረገው ነገር እንደማይኖር እና እንደሌለም አስታውቀዋል። በክልሉ የተፈጠረው ችግር እየጎዳው ያለው ክልሉን ነው ብለዋል። የፌዴራል መንግሥት ለሰላም ሁልጊዜ ዝግጁ መኾኑንም ገልጸዋል። አማራጫችን በመከባበር ላይ የተመሠረተ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት መገንባት ነው ብለዋል።ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት መንግሥት እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።

የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመኾን ኢትዮጵያን ማጽናቱንም ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመኾን አሁን ያለውን ሥርዓት መፍጠሩንም ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ የተሳሳተ ትርክት እንዲስተካከል ይጠይቃል ያሉት አቶ አሕመድ መንግሥት ጥያቄውን ይቀበላል፣ እንዲፈታም ይሠራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን ሕዝብ የጋራ ፍላጎት አንድ ላይ የያዘ የጋራ መተሳሰሪያ ያስፈልገናል ብለዋል። ቋንቋ ፣ ባሕል እና ሃይማኖት ልዩነት መኖር ፀጋ መኾኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን የደም ማንነት ያስተሳሰራቸው አንድ ናቸውም ብለዋል። ኢትዮጵያ ፀንታ እንድትኖር ያደረገው ጠንካራ ትስስር ያለው ሕዝብ በመኖሩ ነው ብለዋል አቶ አሕመድ።

የልማት ሥራዎች ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች መኾናቸውንም ገልጸዋል። የሕገ መንግሥት ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል። በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉዳዮች ሰፊ ውይይት እንደሚደረግበትም ተናግረዋል። የጋራ ሕገ መንግሥት ለመገንባት በሰከነ መንገድ መወያየት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ተሳትፎ ያለበት መፍትሔ ማበጀት ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም አጨቃጫቂ የኾኑ ጉዳዮችን ሰከን ብሎ በመወያየት መፍታት ይገባል ብለዋል። የፍትሐዊ የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን ያነሱት ሚኒስትሩ በአማራ ክልል የመንገድ ችግሮችን ለመፍታት እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የልማት ሥራዎችን ለመሥራት የጸጥታ ሁኔታውን አስተማማኝ አድርጎ መጠበቅ ይገባል ብለዋል። የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጦ ያልተገነቡ ሥራዎች እየታዩ አቅም በፈቀደ መልኩ ይሠራሉ ነው ያሉት። የፌዴራል መንግሥት ችግሮችን በውይይት የመፍታት ፍላጎት አለው ያሉት አቶ አሕመድ የሕግ በላይነት ግን መረጋገጥ አለበት ብለዋል። “የፌዴራል መንግሥት ከማንም ጋር በሰላም ችግሮችን የመፍታት ፍላጎት አለው” ነው ያሉት።

የወረታ የደረቅ ወደብ ፣ የጋፋት የብረታብረት ኢንዱስትሪ እና ሌሎች ጥያቄዎች እንዲፈቱ ይሠራልም ብለዋል።

የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎች ሕጋዊ በኾነ መንገድ በዘላቂነት እንዲፈቱ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል። በአማራ ክልል የተፈጠረው ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ የሕዝብ እገዛ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መኾናቸውን ያነሱት አቶ አሕመድ የሰላም ውይይት ሲባል ግን ሕግ ሲከበር መኾን አለበት ነው ያሉት። መንግሥት የአማራ ክልልን በሕግ የመምራት ኀላፊነት እና ግዴታ እንዳለበትም ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም የማስጠበቅ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ ነው፣ አሁንም የተሻለ ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleክልሉ ችግር በገጠመው ጊዜ ሁሉ “የአንዳችን ችግር የሌላችንም ነው” በማለት በጋራ ለሠሩ መሪዎች ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ምሥጋና አቀረቡ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በናሚቢያው ፕሬዚዳንት ሀጌ ጌንጎብ ሕልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ::