ክልሉ ችግር በገጠመው ጊዜ ሁሉ “የአንዳችን ችግር የሌላችንም ነው” በማለት በጋራ ለሠሩ መሪዎች ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ምሥጋና አቀረቡ።

18

ባሕር ዳር: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ ከእርሳቸው ጋር ተገኝተው ሕዝባዊ ውይይቱን ለመሩት የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጦፌ ሙሁመድ እና ለመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተሥፋየ በልጂጌ ነው የክብር ካባ ያለበሱት።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ “ወንድሜ ሙስጦፌ በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩል ተከብረው እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ እና እንዲኖሩ ያስቻሉ መሪ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

አማራ ክልል ችግር በገጠመው ጊዜ ሁሉ “የአንዳችን ችግር የሌላችንም ነው” በማለት ክልሉ ሰላም እንዲያገኝ በጋራ የሚሠሩ ሰው ስለመኾናቸውም ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ገልጸዋል። ዛሬም “ሰላም የለውም እየተባለ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ወደሚነዛበት ክልል በመዝለቅ የሕዝቡን ጥያቄ በመስማታቸው እናመሠግናቸዋለን” ብለዋል። የክብር ካባውንም በሕዝብ ወኪሎች ፊት አልብሰዋቸዋል።

ሌላው የክብር ካባ የለበሱት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋየ በልጅጌ ናቸው። ሚኒስትሩ የአማራ ክልል ሕዝብ ችግር የሁላችንም ችግር ነው በማለት ወደ ባሕር ዳር ዘልቀው በሕዝብ ፊት በመቆም ጥያቄዎችን ተቀብለዋል። ጥያቄዎች በውይይት ተፈትተው የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንዲመለስ እንደሚሠሩም ገልጸዋል። በዚህ ወቅት የክልሉ ሕዝብ የገጠመውን ችግር በመረዳት ወደቦታው መጥተው ለዘላቂ መፍትሔው በጋር የሚሠሩ ስለመኾኑ ነው የክብር ካባው የተበረከተላቸው።

ሁለቱም መሪዎች በአማራ ክልል ሕዝብ ስም ለተሰጣቸው ክብር አመሥግነዋል። ሕዝቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላሙን አግኝቶ በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት እንዲገባ በአንድነት እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የገጠመንን የችግር አዙሪት ለመሻገር የጋራ ርብርብ ያስፈልገናል” ርእሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ
Next article“የፌዴራል መንግሥት ከማንም ጋር በሰላም ችግሮችን የመፍታት ፍላጎት አለው” አቶ አሕመድ ሽዴ