
ሰቆጣ: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝባዊ አንድነትን እና ሰላምን ለማረጋገጥ ያለመ የሰላም ውይይት በሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ “የሌላው ችግር የኛም ችግር ነው ብለን ለጋራ መፍትሔ መቆምን አባቶቻችን በዓድዋ ያሳዩን ሃቅ ነው” ብለዋል።
ከአባቶች የወረስነውን አብሮነት እና ወንድማማችነት ማጠናከር እንጅ ልናላላው አይገባም ነው ያሉት። ርእሰ መሥተዳድሩ “ይህንን ወንድማማችነት ለማሳየት በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ሰቆጣ የኦሮምያ ክልል መንግሥት በ320 ሚሊዮን ብር የአዳሪ ትምህርት ቤት ለመገንባት ከሶስት ሳምንት በፊት አስጀምሯል” ብለዋል። ያስጀመርነውን ዘመናዊ አዳሪ ትምህርት ቤትም በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀን እናስረክባለን ነው ያሉት።
የዋግ ኽምራ ሕዝብ ሰላም ወዳድ መኾኑን አሳይቷል፤ ይህንንም አጠናክራችሁ ቀጥሉ ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ ውድ ህይወታቸውን እየከፈሉ ላሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ምሥጋና አቅርበዋል።
ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መቆም ማለት ሀገርን ማዳን ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የገጠመንን የችግር አዙሪት ለመሻገር በጋራ ለሰላም እና ለብልጽግና መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!