“የሐሰት ትርክቶችን በማረም የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ሊያረጋግጥ የሚችል አርበኛ ትውልድ መገንባት ይገባል” አቶ መለሰ ዓለሙ

9

ደብረ ማርቆስ: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።

ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ለሁለንተናዊ ብልፅግና በሚል መሪ ሃሳብ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን እና ከደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በደብረ ማርቆስ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት በማስቆም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ለጋራ ሀገራዊ ችግሮች መፍትሔ ለማስቀመጥና ሕዝባዊ አንድነት ለመፍጠር ያለመ ውይይት ነው የተካሄደው።

ውይይቱ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መለሰ ዓለሙ የመነሻ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በደብረ ማርቆስ እና አካባቢው በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት መቸገራቸውን አንስተዋል። የትምህርት ተቋማት መደበኛ ሥራቸውን ባለመጀመራቸው ልጆቻቸው መማር እንዳልቻሉ፤ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ነው የተናገሩት።

ነዋሪዎቹ በየአካባቢው የተከሰተውን የሰላም እጦት ችግሮችን በመለየትና በማረም ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ማረም ይገባልም ብለዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ በጸጥታ ችግር ምክንያት ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል። አሁን ላይ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግም ሁሉም የኅበረተሰብ ክፍል የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ቴንኩዌይ ጆክ ሁላችንም እኩል ተጠቃሚ የምንኾንባት ኢትዮጵያን መገንባት ይገባል ብለዋል። ከምንም በላይ ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልምና ሁሉም አካል በጋራ ለሰላም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባናል ነው ያሉት።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) በበኩላቸው መንግሥት በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል። መንግሥት ከሚያከናውነው ሥራ ባለፈ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት ዶክተር እዮብ። የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መለሰ ዓለሙ ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ምንጩን መለየትና የመፍትሔ አማራጮችን ማስቀመጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ይመለሱ ዘንድ ቅድሚያ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡በቀጣይም የሚነሱ የሐሰት ትርክቶችን በማረም የአንድነት ትስስራችንን ማጠናከርና የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ሊያረጋግጥ የሚችል አርበኛ ትውልድ መገንባት ይገባል፡፡

መንግሥት በሕዝቡ የሚነሱ ሁለንተናዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከሁሉም አስቀድሞ ሰላም እንዲኾን እና ጥያቄዎች እንዲፈቱ እንደሚፈልጉ የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።
Next article“የገጠመንን የችግር አዙሪት ለመሻገር የጋራ ርብርብ ያስፈልገናል” ርእሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ