
ደብረ ታቦር: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።
“ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ መልእክት ሕዝባዊ ውይይት በደብረ ታቦር ከተማ ተካሂዷል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ሀገርን አፍርሶ ከመገንባት ሠባራውን እየጠገኑ ማስቀጠል ይሻላል ብለዋል።
በጦርነት የሚሠራ ሥራ ውጤታማ አለመኾኑን ገልጸዋል። ሰላም ከምንም በላይ ነው ብለዋል። አባቶቻችን ብሔር ሳይለዩ በሀገር ፍቅር ስለተነሱ ሀገር አቆይተዋል ያሉት ነዋሪዎቹ ለሰላም በአንደነት መነሳት ይገባል ብለዋል። ኢትዮጵያ ከጥፋት የዳነችው በአንድነት በተሠራው ሥራ መኾኑንም ገልጸዋል። የቋንቋ ልዩነት ለግጭት ምክንያት ሊኾን አይገባም፣ ኢትዮጵያዊነት የጋራ መተሳሰሪያችን ነው ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ያነሳቸው የሕገ መንግሥት፣ የማንነት እና የወሰን፣ የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ጥያቄዎች እንዲፈቱለት ይፈልጋል ነው ያሉት።
ዜጎች በእኩልነት የሚከበሩባት ኢትዮጵያን እንሻለንም ብለዋል። ግጭትን የሚያባብሱ ሚዳያዎች ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል ያሉት ነዋሪዎቹ በድሎት እየኖሩ ግጭት እንዲጠመቅ የሚያደርጉ ሚዲያዎች በቀላሉ ሊታዩ እንደማይገባም ነው ያስገነዘቡት።
መካላከያ ሠራዊት ልጃችን ነው፣ ብሔር የለውም፣ ያለው ሀገር ነው፣ የቆመው ሀገር ለማቆም ነው መከላከያን እንወደዋለን ብለዋል። በአማራ ክልል የተፈጠረው ችግር ብዙ የዳቦ ጥያቄ እንዳለበትም ተናግረዋል። የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲጠናቀቁ፣ የኑሮ ውድነት እንዲፈታም ጠይቀዋል።
ለዘላቂ ሰላም ውይይት ማድረግ አዋጭ መኾኑንም ገልጸዋል። በደብረ ታቦር ከተማ እና በአካባቢው ያሉ የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱም ጠይቀዋል። ለሀገር ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገውን ሕዝብ ሕልውናውን የሚፈታተኑ ችግሮቹ ሊፈቱለት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ በችግር ውስጥ ኾኖ እንኳን በሕግ አምላክ ሲባል የማይንቀሳቀስ ለሕግ ተገዥ ነው፣ ለሕግ ተገዥ የኾነው ሕዝብ ሕግ ሊከበርለት ይገባል ነው ያሉት።
በከተማዋ የአዳሪ ትምህርት ቤት እንዲሠራ፣ ለወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥሩ ኢንዱስትሪዎች እንዲገነቡም ጠይቀዋል። ለወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥሩ ኢንዱስትሪዎች በተገነቡ ቁጥር ለግጭት የሚነሱ ወጣቶች ይቀንሳሉ ነው ያሉት።
ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለሕዝብ ሰላም መስጠት ይገባል፣ ከሁሉም አስቀድሞ ሰላም እንዲኾንልን፣ ቀጥሎ ጥያቄዎች እንዲፈቱልን እንፈልጋለን ብለዋል። በሰላም እጦት ምክንያት ግብር ከፋይ ነጋዴዎች እየተሰደዱ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በምጣኔ ሃብት የተጎዳውን አካባቢ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
የሰላም ኮሜቴ ተቋቁሞ በግጭት ተሳታፊ የኾኑ ወንድሞች እንዲገቡ በማድረግ የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ለአርሶ አደሮች በቂ የግብዓት አቅርቦት እንዲቀርብላቸውም አንስተዋል። ጥያቄዎችን እየፈቱ መሄድ ካልተቻለ ወደ ተባባሰ ችግር እንገባለንም ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት አይደራደርም ያሉት ነዋሪዎቹ ፍላጎቱ ጥያቄዎች እንዲፈቱለት እና በእኩልነት እንዲኖር መኾኑንም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!