“ወጣቱ በተሳሳተ ትርክት እና በማኅበራዊ ሚዲያ በሚሰራጭ አሉባልታ ሳይፈታ የሰላሙ ባለቤት ሊኾን ይገባል” ዓለሙ ስሜ (ዶ.ር)

21

ገንዳ ውኃ: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።

“ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና በሚል መሪ መልእክት በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ እና የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የዞን እና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ከዞኑ የተወጣጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ አባል ዓለሙ ስሜ (ዶ.ር) የመቻቻል፣ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት እና የወንድማማችነት እሴቶችን የበለጠ በማጎልበት ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስረከብ ይገባል ብለዋል።

ልማቷ፣ ሰላሟ፣ አንድነቷ እና ኅብረ ብሔራዊነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማሻገር ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የጸጥታ መዋቅሩ ተግባር እና ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን የሰላም ወዳዱ ማኅበረሰብ ጭምር ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።

በመኾኑም ማኅበረሰቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመኾን ለሰላሙ ዘብ ሊቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ከአሁን በፊት ሲያደርጉት የነበረውን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት።

“ወጣቱ በተሳሳተ ትርክት እና በማኅበራዊ ሚዲያ በሚሰራጭ አሉባልታ ሳይፈታ የሰላሙ ባለቤት ሊኾን ይገባልም” ብለዋል።

በጠመንጃ ሥልጣን የመያዝ አባዜን በማስወገድ ችግሮችን በውይይት እና በምክክር መፍታት እንደሚገባም አስረድተዋል።

“ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስረከብ አለብን” ያሉት ዶክተር ዓለሙ ስሜ ነጻ፣ ገለልተኛ እና በዕውቀት የሚመሩ ተቋማትን በመገንባት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሁላችንም የሰላም ሐዋሪያ ልንኾን ይገባል” የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ
Next articleከሁሉም አስቀድሞ ሰላም እንዲኾን እና ጥያቄዎች እንዲፈቱ እንደሚፈልጉ የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።