
ጎንደር: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።
“ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ሕዝባዊ ውይይት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
ሕዝባዊ ውይይቱን የመሩት የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ የአማራ ሕዝብ የወሰንና ማንነት፣ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች በሰላም የመኖር መብት እና ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች እንዳሉት ይታወቃል ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው በውይይት እና በመነጋገር እንደኾነም ጠቁመዋል።
ክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ሰፊ ውይይቶች እየተደረጉ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል ነው ያሉት። አሁንም ወደ ሰላማዊ አማራጮች መመለስ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ በባለፈው ዓመት ከ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ የለማ ቢኾንም በዚህ ዓመት ግን በክልሉ ያለው የሰላም እጦት ያለፈውን ዓመት ስኬት ማስቀጠል አልተቻለም ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ለጎንደር ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክትም “ሁላችንም የሰላም ሐዋሪያ ልንኾን ይገባል” ብለዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ሰላምን ማስፈን የጋራ ኀላፊነት በመኾኑ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በመንግሥት ዘንድ ተይዘው እየተሠራባቸው መኾኑን ያነሱት አቶ ይርጋ በሕዝብ ጥያቄ ሰበብ ክልሉን የብጥብጥ ቀጣና ለማድረግ የሚሰሩ ሁሉ ኀላፊነት የማይሰማቸው ናቸው ብለዋል።
የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙም እየተሻሻለ የመጣውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ማድረግ ከሕዝብና ከመንግሥት ይጠበቃል ነው ያሉት።
በሕዝባዊ መድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ ለሰላም ሁላችንም ልንሠራ ይገባል፤ ግጭትና ጦርነት ትርፉ ውድመት በመሆኑ የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ሰላም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በየመድረኩ በጭብጨባ የሚያበቃ ሃሳብ እና ንግግር ከመሰንዘር ባለፈ ሰላምን ሊያመጡ የሚችሉ ተግባራዊ ምላሾች መስጠት ይገባናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሳ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!