
ደባርቅ: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ አሥተዳደር “ፈተናዎችን ተሻግረን የኢትዮጵያን ልዕልና በጋራ አንሠራለን፤በአንድነት ስንቆም ህልውናችንን እና ክብራችንን እናስጠብቃለን” በሚል መሪ መልእክት በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ ከኹሉም ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሕዝባዊ ውይይት ተደርጓል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጸጋዬ ማሞ፤ የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል አብርሃም ማርሻሎ፤ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ፤ የሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በመድረኩ ተገኝተዋል።
በመድረኩ እንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አበባው አዛናው ከፌዴራል እና ከክልል የመጡ እንግዶችን ወደ አካባቢው በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ደባርቅ እና አካባቢው የኹሉም የአየር ንብረት ባለቤት፣ የቱሪስት መዳረሻ የኾነ፤ አስተዋይ እና አርቆ አሳቢ ሕዝብ ያለበት ዞን መኾኑን በመድረኩ ለተገኙት የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች አብራርተዋል።
አቶ አበባው በአማራ ክልል የጸጥታ ችግር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከተማዋ በኮማድ ፖስት ሥር ኾና እየተዳደረች እንደምትገኝ ተናግረዋል። የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ከማኅበረሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ የአካባቢውን ሰላም እስካሁን መጠበቅ እንደተቻለም ጠቅሰዋል።ለዚህም ተሳትፎ ለነበራቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ምሥጋና አቅርበዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ የዞኑ ሕዝብ እንደ ሀገር ለውጥ እንዲመጣ ከመላ ኢትዮጵያዊያን ጋር ከፍተኛ ትግል አድርጓል ብለዋል። በትግሉ ያመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚጥሩትንም እየታገለ የመጣ እና እንደ ሀገር እና እንደ ክልል የተፈጠሩ ችግሮችን ሚዛን ላይ ቆሞ የሚያይ፥መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮችን እንዲስተካከሉ በመርህ የሚታገል ሕዝብ መኾኑን አሳውቀዋል።
ዲያቆን ሸጋው የሰሜን ጎንደር ዞን ካለፈው ጦርነት ከደረሰበት ጉዳት ሳያገግም በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በማኅበረሰቡ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የጸጥታ ችግር ሲፈጠር በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎችም ችግሮች እንደነበሩ ያነሱት ዋና አሥተዳዳሪው የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በተኩስ መሀል ገብተው ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ሰላምን ለማስፈን በተሠራው ሥራም ዞኑ አሁን ላይ የተሻለ ሰላም ያለበት አካባቢ ኾኗል ነው ያሉት።
በሕዝባዊ ውይይቱ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል ጸጋዬ ማሞ በሰላሙ ጉዳይ ስለደባርቅ እና አካባቢው የሰማነው እና በዐይናችን ያየነው ነገር በጣም የተለያዬ በመኾኑ በጣም ደስ ብሎኛል ብለዋል።ለውጤቱም ባለቤቱ ማኅበረሰቡ በመኾኑ ምሥጋና ይገባችኋል ነው ያሉት።
ኹላችንም የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚዎች የአማራ ክልል የሰላም ጉዳይ ስለሚያገባን እና ስለሚመለከተን በኹሉም አካባቢዎች ተንቀሳቅሰን ውይይት እያደረግን ነውም ሲሉ አስረድተዋል።
አቶ ጸጋዬ ማሞ ወደ አካባቢው ሲደርሱ የዞኑ እና የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ላደረገላቸው መልካም አቀባበል እንዲሁም መስተንግዶ ምሥጋና አቅርበዋል።
በውይይቱ የመድረኩ ተሳታፊዎች ለሰላም እጦት መነሻ ናቸው፤ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን አካባቢያዊ፣ ዞናዊ፣ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ዘጋቢ :-አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!